
ባሕር ዳር: ነሐሴ 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
ኢትዯጵያ እያገባደደችው የሚገኘው ዓመት እጅግ ስኬታማ ኾኖ እየተጠናቀቀ መኾኑን የገለጹት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) በተለይም በዓመቱ ውስጥ ግዙፍ እና በመካከለኛ ደረጃ የሚታዩ ፕሮጀክቶችን ያጠናቀቀችበት ዓመት ነው ብለዋል::
ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የቆዩ መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት እና ዘላቂ ዕድገትን ለማስፈን ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መግባቷም በመግለጫው ተመላክቷል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሀገሪቱ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን ለመፍጠር፤ የንግድ ሥራዎችን የሚያሳልጡ የሚያቃልሉ እና ውጤታማነትን የሚያመጣ እንደኾነ ነው የገለጹት።
የንግድ እና ኢንቨስትመንት አካባቢዎችን ማሻሻል፣ የሴክተር ሪፎርም በመባል የሚታወቀውን የዘርፉን ምርታማነት እና ተወዳዳሪነትን የማሳደግ ብሎም የማስፈፀም አቅምን ማጎልበትን ማዕከል ያደረገ እንደኾነም ተመላክቷል::
እንደ መንግሥት ኮሙኒኬሽን መግለጫ ማሻሻዎቹ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን እና የንግድ ዕድሎችን በማስፋት የግል ሴክተሩ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ጉልህ ሚና የሚያሳድጉ በመኾናቸው ለውጤታማነቱ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንዳለም ተመላክቷል::
አሁን ባለው ሁኔታም በማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ መንግሥት የወሰደው የማሻሻያ እርምጃ የተራራቁ ገበያዎችን ማቀራረብ፣ ኢ-መደበኛ የኾነውን የኢኮኖሚ ሥርዓት ወደ መደበኛ የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲቀየር ብቻ በመደረጉ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ የለም ነው ያሉት።
በሕገወጦች ላይም ተገቢ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ።
ሰላም እና መረጋጋት በሌለበት ሁኔታ ምንም ዓይነት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማድረግ ስለማይቻል መንግሥት የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ ይቀጥላልም ተብሏል::
በሳምንታዊ መግለጫው ኢትዮጵያ በመጠናቀቅ ላይ ባለው ዓመት ከነሐሴ 29/2016 ዓ.ም እስከ ጳጉሜን 1/2016 ዓ.ም አንደኛውን የአፍሪካ የከተሞች ፎረም እንደምታስተናግድ ተጠቁሟል::
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!