
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም የኔትወርክ ሽፋን ተደራሽ ባልነበረባቸው ገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች 100 የሞባይል ኔትወርክ ኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ግንባታን አጠናቅቆ አገልግሎት አስጀምሯል።
አገልግሎቱ በ305 የገጠር ቀበሌዎች እና መንደሮች ለሚኖሩ ከ900 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ አባላትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ፍሬሕይዎት ታምሩ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን በቅሎ ሰኞው ወረዳ በመገኘት የፕሮጀክቱን የመጀመርያ ምዕራፍ መጠናቀቅ አብስረዋል፡፡
ዋና ሥራ አሥፈፃሚዋ ራቅ ባሉ የገጠር አካባቢዎች ላይ ለመገንባት የሚገጥሙ እንደ መሬት አቀማመጥ፣ የመንገዶች ያለመኖር፣ የኀይል አቅርቦት እጥረት ያሉ ተግዳሮቶች ሳይበግሩት ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱን አብራርተዋል፡፡
የገጠር ሞባይል አገልግሎቱ በቀላሉ የኔትወርክ አቅምን በማሳደግ ከ2G እስከ 3G እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ በማዘመን የ4G አገልግሎት መስጠት የሚያስችል፤ በሶላር ኀይል የሚሠራ፤ የአካባቢ ብክለትን የማያስከትል፤ ዘመናዊ ገጽታ የተላበሰ ነው ብለውታል።
ይህ የገጠር ኮኔክቲቪቲ አገልግሎት እውን መኾን ኢትዮ ቴሌኮም በአፍሪካ ደረጃ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ካደረጉ ጥቂት ኦፕሬተሮች አንዱ እንደሚያደርገው አስረድተዋል፡፡
ዋና ሥራ አሥፈፃሚዋ ይሄን አገልግሎት ለማግኘት በአማካይ 20 ኪሎ ሜትር ያደርጉት የነበረውን ጉዞ ያሳጠረ፤ የገጠሩን ማኅበረሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደረገ ነው ብለዋል።
ይህ አገልግሎት በገጠራማ የሀገሪቱ ክፍል የሚኖረው የማኅበረሰብ ክፍል መሠረታዊ የቴሌኮም አገልግሎት እንዲያገኝ ከማስቻሉም በተጨማሪ በሕዝቦች መካከል የሚኖረውን ኢ- ፍትሐዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ስብጥርን ለማጥበብ እንደሚያስችል አስገንዝበዋል፡፡
ቴክኖሎጅው በትምህርት፣ በጤና እና በግብርና የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ ለዜጎች ኢኮኖሚ ዕድሎችን በመፍጠር የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስረድተዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብም ከእንግልት እንደተገላገለ ገልጿል፡፡ አገልግሎቱ ከቤተሰብ ጋር በቀላሉ ለመገናኘት እንዳስቻላቸውም ነው ለአሚኮ የገለጹት፡፡ የብድር እና የቁጠባ አገልግሎትን በቀላሉ ለማግኘት እንደሚያስችላቸውም ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል ኪሮስ- ከደቡብ ኢትዮጵያ ወላይታ ዞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!