
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ.ር) ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻ ትግበራ መግባቷን ያወሱት ሚኒስትሩ፤ ይህ ማሻሻያ ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የኢኮኖሚ ዕድገት ለምታደርገው ሽግግር አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።
ማሻሻያው የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን ለመፍጠር፣ የዘርፎችን ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮችን ለማስተካካል የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አካታችና ዘላቂ ዕድገት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባት፣ የመንግሥት ገቢን ለማሳደግ እና በሃገር ውስጥ ምርት ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ ያግዛል ብለዋል።
ማሻሻያው በታቀደለት አግባብ እየተተገበረ እንደሚገኝ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ውዥንብር በመፍጠር ለገበያ አለመረጋጋት ምክንያት እየሆኑ ያሉ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ማሻሻያው በግብታዊነት እንዳልተደረገ እና ባለ ድርሻ አካላትን በስፋት እንዳሳተፈ ጠቅሰው፤ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚፈልጉ ወገኖች ግን ጉዳዩን በተዛባ መንገድ እያራገቡት እንደሆነ ገልጸዋል።
መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የስንዴ፣ የሩዝ፣ የአትክልትና ፍራ ፍሬ ምርቶች ላይ ሲሠራቸው የቆዩ ሥራዎች የማሻሻያው አካል እንደሆኑ ተናግረዋል።
በማሻሻያው ትግበራ የወጭ ምርቶችን የሚያመርቱ አርሶ አደሮች እና አምራች ኢንዱስትሪዎችም ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ነው ዶክተር ለገሠ የገለጹት።
ኢቢሲ እንደዘገበው በትግበራው ኢ-መደበኛ የሆነው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወደ መደበኛ እንደሚገባ እና በውጭ ምንዛሪ እጥረት ከአቅም በታች እያመረቱ ያሉ ኢንዱስትሪዎችም በቂ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!