”የዋጋ ንረት በክልሉ ሕዝብ ላይ ተጨማሪ ችግር እንዳይኾን ኀላፊነት ይዘን መሥራት ይጠበቅብናል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

57

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሕገ ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ መከላከል እንዲሁም የዋጋ ማረጋጋት ጥምር ግብረ ኀይል በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና በዋጋ ማረጋጋት ላይ ምክክር አድርጓል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በምክክሩ ላይ ሀገሪቱ ያጋጠማትን የምጣኔ ሃብት ስብራት ለማስተካከል እና የሃብት ክምችትን ለማሻሻል ሁለንተናዊ ጠቀሜታ እና ጽንሰ ሃሳብ የያዘ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል። ማሻሻያውን በተሟላ ገጽታው ከመረዳት ይልቅ ከምንዛሬ መሻሻል ጋር ብቻ ያለውን በመመልከት የተዛባ ግብይት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ተዋናዮችን መፍትሄ ለመስጠት ውይይት ማስፈለጉን ገልጸዋል።

ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ከፌደራል መንግሥት ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ የተቋቋመ የግብይት እና የጸረ ኮንትሮባንድ ግብረ ኀይል በሥራ ላይ መኾኑን ተናግረዋል።

የግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርት እንዲሁም ምርታማነትን በማሻሻል አቅርቦትን ማሳደግ፤ ግብይቱ ጤናማ እንዲኾን ሕጋዊ የግብይት ሥርዓት መፈጠሩን መከታተል እና ማመቻቸት፤ ግብይቱ የሚመራበትን መሠረተ ልማት ማስተካከል የግብረ ኀይሉ ሥራዎች ናቸው ብለዋል።

በሌላ በኩል ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ጋር ተያይዞ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲመራ በመንግሥት ሲወሰን ተገቢ ያልኾነ የዋጋ ጭማሪ እና የኑሮ ውድነት ምልክቶች እየታዩ ነው፤ ይህንን የዋጋ ጭማሪ እና የኑሮ ውድነት በሥርዓት መምራት ይገባል፤ ለዚህም ኢኮኖሚያዊ ያልኾኑ ምክንያቶች በሥርዓት ተይዘው የምርት እና አገልግሎት የአቅርቦት ችግር ካለ የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ እጥረቶችን በመፍታት ለማስተካከል፣ ገበያውን ለማረጋጋት እና ለመቆጣጠር ውይይቱ አስፈላጊ እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት።

“የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነትን ለመከላከል የክልሉ ንግድ ቢሮ ከፌዴራል ጋር በየቀኑ እየተወያየ እየተመራ ነው፤ እኛም በዚያው ልክ እየተወያየን ችግሮችን መፍታት አለብን፤ የዋጋ ንረት ጉዳዩ ከጸጥታ ችግሮቹ ጋር ተደማምሮ በክልሉ ሕዝብ ላይ ተጨማሪ ችግር እንዳይኾን ኀላፊነት ይዘን መሥራት ይጠበቅብናል” ነው ያሉት፡፡ ተልዕኮውንም ወስደው በየመዋቅራቸው በቅንጅት በመሥራት የተደራጀ የአቅርቦት፣ የሕግ የማስከበር እና የማረጋጋት ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።

በውይይቱ የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮን ጨምሮ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ፣ የጉሙሩክ ኮሚሽን፣ የገቢዎች፣ የፖሊስ፣ የፍትሕ የሰላም እና ጸጥታ፣ የግብርና፣ የእንሰሳትና አሳ ሃብት ልማት ኤጀንሲ፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ የጤና፣ የማዕድን ሃብት እና የሌሎች ተቋማት መሪዎችም ተሳትፈዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የከተማ ጽዳት እና አረንጓዴ ልማትን በማስተሳሰር እየተሠራ ነው” የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር
Next article“የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ ወደ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ለምታደርገው ሽግግር አመቺ ሁኔታን የሚፈጥር ነው” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት