“የከተማ ጽዳት እና አረንጓዴ ልማትን በማስተሳሰር እየተሠራ ነው” የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር

27

ደብረ ማርቆስ፡ ነሐሴ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር አካባቢ ጥበቃ ጽዳት እና ውበት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ከተማዋን ለነዋሪዎቿ የተመቸ ለማድረግ እና ገጽታዋን ይበልጥ ለማሻሻል እየሠራ ይገኛል፡፡

በከተማዋ ደረቅ ቆሻሻን የሚሠበሥቡ በዘጠኝ ማኅበራት የተደራጁ ከ230 በላይ አባላት በርካታ የአረንጓዴ ልማት እና የመንገድ ጽዳት ሠራተኞች ከተማን ጽዱ እና ውብ ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

የከተማ አሥተዳደሩ አካባቢ ጥበቃ ጽዳት እና ውበት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቸርነት ዓለማየሁ ለአሚኮ እንደገለጹት የነባር ማኅበራትን ቁጥር ከፍ ለማድረግ እና የአባላቱን የላብ መተኪያ እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በደረቅ ቆሻሻ አሠባሠብ ዘርፉ ላይ የአገልግሎት ታሪፍ ማሻሻያ በማድረግ ወደ ተግባር መገባቱን ነው የተናገሩት፡፡

በከተማ አሥተዳደሩ ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ የጽዳት ዘመቻ መደረጉን የተናገሩት ኀላፊው ኅብረተሰቡ የሚያመነጨውን ቆሻሻ በአግባቡ እንዲያስወግድ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ችግኞችን በማፍላት ለአረንጓዴ ልማት ሥራው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኞችን በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች መትከል ስለመቻሉ ተናግረዋል፡፡

የከተማ አሥተዳደሩ አካባቢ ጥበቃ ጽዳት እና ውበት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ ከ9ሺህ 500 በላይ ችግኞችን በማዘጋጀት ለተከላ እንዲውሉ አድርጓል ነው ያሉት፡፡

ችግኞችን መትከል የመጨረሻ ግብ ስላልኾነ ኅብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት ለተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ እንዲያደርግም ኀላፊው አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- መልሰው ቸርነት

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር 378 የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተቋማት ተጠግነው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገለጸ።
Next article”የዋጋ ንረት በክልሉ ሕዝብ ላይ ተጨማሪ ችግር እንዳይኾን ኀላፊነት ይዘን መሥራት ይጠበቅብናል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)