ኅብረተሰቡ ለወረርሽኙ የሚመጥን ጥንቃቄ አንዲያደርግ የምሁራን መማክርት ጉባዔው አሳሰበ፡፡

192
የኮሮና ቫይረሥ ወረርሽኝ ስርጭትና የኅብረተሰቡ ጥንቃቄ በእጅጉ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ሁሉም ዜጋ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በአግባቡ እንዲተገብር በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የምሁራን መማክርት ጉባዔ ጥሪ አቅርቧል፡፡
 
ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የዓለማችን ዜጎችን በፍጥነት ያጠቃው የኮሮና ቫይረሥ ወረርሽኝ ከመገታት ይልቅ እያሻቀበ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያም 44 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ አራት ሰዎች ማገገማቸው መልካም ዜና ቢሆንም በአንድ ቀን ብቻ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ደግሞ አሳዛኝ ሆኗል፡፡ አሐዙ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ይገኛል፡፡ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ምሁራን መማክርት ጉባዔ የጉዳዩን አሳሳቢነት እና መደረግ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች በተመለለከተ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
 
በጥንቃቄ መልዕክቱም ማኅበረሰቡ ለበሽታው የሰጠው ትኩረት አናሳ መሆንና በአጭር ጊዜ የባህርይ ለውጥ ማምጣት አለመቻሉ ቫይረሱን በፍጥነት እንደሚያዛምተው መገንዘብ እንደሚገባ ነው ያሳሰበው፡፡ የመማክርት ጉባኤው ፕሬዝደንት ዶክተር ገበያው ጥሩነህ አሁን ላይ በወረርሽኙ የሚያዙት ቁጥር እያሻቀበ፣ ሞትም እየተከሰተ መሆኑን በማስታወስ የመከላከል ምክረ ሀሳቦችን በአግበቡ መተግበር እንደሚገባ መክረዋል፡፡ ከጥንቃቄ ይልቅ ቸልተኝነቱ የመከላከል ሥራውን አደገኛ ከማድረጉም በላይ የከፋ ችግር ሊያስከትል እንደሚችልም ነው የተናገሩት፡፡
 
በምሁራን መማክርት ጉባኤው የጤና ዘርፍ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ተፈሪ ገድፍ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከእለት ወደ እለት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ቢመስልም በቀጣይ ቁጥሩ ሊያሻቅብ ስለሚችል መጠንቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በሀገሪቱ የምርመራ ቦታዎችን በመጨመር ሲሠራ አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሊገኙ እንደሚችሉ በመግለጽም መዘናጋቱ ዋጋ እንዳያስከፍል መገንዘብ እንደሚገባ መክረዋል፡፡
 
በሽታው ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ የጥንቃቄ ማነስ እየተስተዋለ መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር ተፈሪ የህከምና ባለሙያዎችን ምከረ ሀሳብ መተግበርና ምልክት ሲታይም በፍጥነት ራስን በመነጠል የሚደርሰውን አደጋ መቀነስ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ሳልና ከፍተኛ ሙቀት ሲከሰት ግለሰቦች ራሳቸውን በመነጠል የህክምና እርዳታ እንዲደረግላቸው በማድረግ የበሽታውን መስፋፋት መቀነስ እንደሚችሉም ነው ያስገነዘቡት፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከመገባቱ አስቀድሞ በአማራ ክልል ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ ምክረ ሀሳብ ከማቅረብ ጀምሮ አሁን ክልሉ በትኩረት እንዲሠራ የመማክርት ጉባኤው ከክልሉ መንግስት ጋር በትኩረት እየሠራ መሆኑን ደግሞ ዶክተር ገበያው ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ውስጥ የምርመራ ማዕከላት ቁጥር እንዲጨምርና በአዲስ አበባ ለክልሉ ድጋፍ የሚሆን ማእከል እነዲቋቋም እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
 
ዘጋቢ፡-ሰጠኝ እንግዳው-ከአዲስ አበባ
Previous articleሩሲያ የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት የጣለችውን የእንቅስቃሴ ገደብ የሚጥሱ ሰዎችን ማንነት የሚለይ ካሜራ ተከለች፡፡
Next articleሐሰተኛ 71 የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን የግርጌና የራስጌ ማኅተሞች እያዘጋጀ ሲሰጥ የነበረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡