
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር 378 አነስተኛ የውኃ ተቋማት ተጠግነው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ውኃ እና ኢነርጂ መምሪያ ገልጿል።
በመምሪያው የመጠጥ ውኃ ጥናት እና ዲዛይን ባለሙያ ታደሰ አዳነ፤ በአገልግሎት ብዛት ለብልሽት ተዳርገው የነበሩ 332 የውኃ ተቋማት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ለመጠገን ታቅዶ ሢሠራ መቆየቱን ተናግረዋል።
በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልኾኑ ድርጅቶች የበጀት ድጋፍ 378 አነስተኛ የውኃ ተቋማትን ጠግኖ ለአገልግሎት በማብቃት ከዕቅድ በላይ መከናወኑን አስረድተዋል።
በዚህም ከ110 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዳግም የንፁህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ለውኃ ተቋማቱ ጥገናም 50 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ጠቅሰው ኅብረተሰቡ የውኃ ተቋማትን በአግባቡ ሊጠብቅ እና ሊንከባከብ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በቀጣይም የአርቢት፣ ላልኪው፣ ደብረ ወይላ እና መሸሃ በሚባሉ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ አካባቢዎች እየተሠራ ያለውን የውኃ ተቋማት ግንባታ በአጭር ጊዜ ለአገልግሎት እንዲበቁ ርብርብ እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል።
በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የ01 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሳሙኤል በሬ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው የንፁህ መጠጥ ውኃ የሚያገኙበት ቧንቧ በመበላሸቱ ለሰባት ወራት የወንዝ ውኃ ለመጠቀም ተገደው እንደነበር አውስተዋል።
በአኹኑ ወቅት በአካባቢያቸው የሚገኘው ቧንቧ ተጠግኖ ለአገልግሎት በመብቃቱ ዳግም የንፁህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የውኃ ተቋሙን በአግባቡ ለመጠቀም በአካባቢው ካሉት ነዋሪዎች ጋር እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ሌላው ነዋሪ አቶ ሞገስ ኃይሌ ”የንፁህ መጠጥ ውኃ ተቋማት መጠገን በመቻሉ የእናቶችን እንግልት እና ስቃይ ያስቀረ ነው” ብለዋል።
ቧንቧው ሲበላሽ በርቀት ከሚገኝ ወንዝ ውኃ ለማምጣት ልጆቻቸው ጭምር ከትምህርት ቤት አርፍደው እና ቀርተው ይቀዱ እንደነበር አስታውሰዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ውኃ እና ኢነርጂ መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የንፁህ መጠጥ ውኃ ሽፋን 47 በመቶ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!