
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው “የጎንደር አብያተ መንግሥታት ሲባል ዋናው ግቢ ብቻ አይደለም፣ ሌሎች ዘጠኝ ቅርሶችንም ይጨምራል” ይላሉ፡፡ ጉዛራን፣ ጎርጎራ ሲስንዮስን፣ ቁስቋምን፣ ጥምቀተ ባሕሩን፣ ደብረ ብርሃን ሥላሴን ሁሉ የሚጨምር መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የጎንደር አብያተ መንግሥታት ለረጅም ዓመታት እድሳት ሲደረግለት መቆየቱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ሁሉን አቀፍ ጥገና ግን ሳይደረግለት መቆየቱን ነው ያስታወሱት፡፡
በ2012 ዓ.ም ቅርሱ ያለበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ጥናት በማድረግ መጠገን አለበት የሚል ውሳኔ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣኑ መወሰኑንም አንስተዋል፡፡ በቅርስ ጥገና ዘርፍ በታወቁ እና ልምድ ባላቸው አካላት ጥናት እንዲደረግ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ ጥናቱ ጥገና፣ ምድረ ግቢ ማስዋብ እና የመብራት አገልግሎት እንዲኖረው ማድረግ ላይ ትኩረት ያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ቤተ መንግሥቱ ለጎንደር እንቁ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በቀንና በማታ ጎልቶ እንዲታይ መደረግ አለበትም ብለዋል፡፡ ቤተ መንግሥቱ በገበታ ለትውልድ አማካኝነት በ2015 ዓ.ም ጥገና እንዲደረግለት ተወስኖ የነበረ ቢኾንም በነበሩ ችግሮች ምክንያት መዘግየቱንም አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ አብያተ መንግሥታቱ ታሪካቸው ተጠብቆ፣ ለጎብኚዎች ምቹ እየኾኑ፣ ጥሩ መዳረሻ እንዲኾኑ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በእድሳቱ ታሪኩን በሚገባ የሚገልጹ ሥራዎች እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ ከመጠገን፣ ከመንከባከብ እና ከመጠበቅ ባለፈ ቅርሶችን ማልማትም ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ቅርስ ማልማት ለጎብኚዎች ምቹ አድርጎ በዚያው እንዲቆዩ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ጎንደር ላይ በአብያተ መንግሥታቱ እድሳት እና ጥገና ውስጥ ለዓመታት ሢሠሩ የነበሩ ብቁ ባለሙያዎች በመኖራቸው ለቅርስ ጥገናው አመች መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ረጅም ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች የጎዛራ ቤተ መንግሥትን ጥገና በጥሩ ሁኔታ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ቅርስ ጥበቃና ጥገና ላይ ባዕድ ነገር አይገባም ያሉት ዳይሬክተሩ ጥገናው የሚካሄደው ባለሥልጣኑ ቁጥጥር እያደረገበት፣ በአብያተ መንግሥታቱ ያሉ ባለሙያዎችም እየተከታተሉት መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡
ሥራው በፍጥነት ሲከወን የቀደመ ታሪኩን እና ጥራቱ ተዘንግቷል ማለት አለመኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ጥገናውን የሚያፈጥነው ዘመኑ የደረሰበት ቴክኖሎጂ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ለጎንደር አብያተ መንግሥታት የሚቆረቆሩ እድሳቱ ምን ይኾን እያሉ ይጨነቁ ይኾናል፣ ነገር ግን ምንም የሚቀየር የለም፣ ታሪኩ ተጠብቆ ነው የሚሠራው፣ ይሄን ለሕዝብ ግልጽ እያደረግን እንሄዳለን ነው ያሉት፡፡ በወሬ ስጋት በጥገናው የሚጠራጠሩ ወገኖችንም ማስረዳት ይቻላል ብለዋል፡፡ ሕዝቡ እውነታውን ተረድቶ ፍጻሜውን ማየት አለበት፣ ጥገናው አፍን በእጅ የሚያስጭን ነው የሚኾነው ብለዋል፡፡
በጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገና የቅርስ አጠባበቅ ላይ ምንም ዓይነት ስጋት አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡ በጥንቃቄ እና በጥራት እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡ ከዋናው ቤተ መንግሥት ጥገና በኋላ የጥገና ሥራዎች በሌሎች ቅርሶችም ቀጣይነት እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን በራሱ በጀት የሚሠራቸው ሥራዎች እንደሚኖሩም ገልጸዋል፡፡
ከጎርጎራ እስከ ጎንደር ያለውን ቅርስ በማልማት ወደ ሥፍራው የሚሄዱ ጎብኝዎችን የጊዜ ቆይታ ማራዘም ይገባል ነው ያሉት፡፡ የቱሪስት ቆይታ በረዘመ ቁጥር ገቢው ከፍ እንደሚልም ተናግረዋል፡፡ የጎንደር አብያተ መንግሥታት ውስጥ ነገሥታቱ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ፣ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ሲከወኑ የነበሩ ሁነቶችን በሚገልጽ መልኩ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ ጣራ እና ግድግዳ ከማሳየት ባለፈ በቤተ መንግሥት ውስጥ የነበረውን ሁሉንም ነገር የሚያሳይ ነገር ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ ለአብነት ይሄ የንጉሡ መኝታ ነበር ከተባለ አልጋ ያስፈልጋል፤ የንጉሡ የግብር አዳራሽ ነው ከተባለ ከመንገር ያለፈ በምስል የሚከስት ሥራ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ በቤተ መንግሥቱም ሙሉ ስዕል የሚሰጥ እና የተሟላ ታሪክ የሚያሳይ ሥራ ይሠራል ነው የተባለው፡፡
ለጎንደር የተገኘውን አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ ጎንደር በሚገባው የተያዘ፣ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ነው ብለዋል፡፡ የጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገና በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሁሉም እንዲተባበር ጠይቀዋል፡፡
የጎንደር አብያተ መንግሥታት ከጉዛራ ሠርጸ ድንግል ቤተ መንግሥት ፣ ጎርጎራ አጼ ሱስንዮስ ቤተ መንግሥት እስከ መናገሻዋ ከተማ ያለውን ታላቁን ቤተ መንግሥት ጨምሮ ሌሎች ቅርሶችን የሚይዝ ነው፡፡ ዓለም ድንቅና ሊጠበቁ ይገባቸዋል ብሎ መዝግቧቸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!