
ባሕር ዳር: ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጉልበታቸው ያልጠና ሕጻናት ይናፍቋታል፤ ርቃ እንደተለየች እናታቸው ይሳሱላታል፤ ቀናት ሳምንታትን፣ ሳምንታት ወራትን አከታትለው ተመልሳ እስክትመጣ ድረስ በስስት ይጠብቋታል። አረጋውያን ይጓጉላታል፤ አበው እና እመው በዓታቸውን ዘግተው ሱባኤ ይገቡባታል፣ ስለ ምድር ሰላም፣ ስለ ሕዝብም ፍቅር ሲሉ አብዝተው ይጸልዩባታል፡፡ ሰማይ የበረከት ዝናብን፣ ምድር ፍሬን እንዲሰጡ ይማጸኑባታል፡፡ ወጣቶች አምላካቸውን አብዝተው ያስቡባታል፤ ዓለማዊውን ትተው ወደ መንፈሳዊ መንገድ ይመለሱባታል፤ በጠዋት መመገብ የለመደች ሆዳቸው፣ በጠዋት መጠጣት የለመደች ጎረሯቸውን ይከለክሏታል፡፡
በዚህች ጊዜ ሕጻናት በጠዋት ተነስተው ምግብ አይቀምሱም፣ እረኞች ከጭብጧቸው ቆርሰው አይጎርሱም፣ ከላሞቻቸው ወተት አይጠጡም፣ ይልቅስ ስንቃቸውን በአገልግላቸው ቋጥረው፣ የውኃ መቅጃ ቅምጫናቸውን አንጠልጥለው፣ ላሞቻቸውን ይዘው ወደ ተራራ ይወጣሉ፣ ወደ ሜዳ ይወርዳሉ እንጂ፡፡
ሕጻናት በዚህች ጊዜ ምግባር ይማሩባታል፣ ደግ ማድረግን፣ መጾምን፣ መመጽዎትን፣ መጸለይን፣ የበደለን ይቅር ማለትን፣ ለፍቅር መበርታትን፣ ከክፉ ነገር መጠበቅን ያያሉ፣ ይማራሉ፡፡
እረኞች ፀሐይ ከአናት አልፋ ወደ ምዕራብ ንፍቅ ካላዘቀዘቀች፣ ጀምበር ሰዓት መድረሱን በርምጃዋ ካልተናገረች በስተቀር አገልግላቸውን አይፈቷትም፣ ስንቃቸውን አይቀምሷትም፡፡ ሰዓት ከእጃቸው የለምና የሰዓቱን መድረስ የሚለኩት ጀምበርን ዓይተው ነው፡፡ ጀምበር ደመና ጋርዷት ብትውል እንኳን ተገልጣ እስኪመለከቷት፣ የሰዓቱን መድረስ እስክትነግራቸው ድረስ በጾም ይቀጥላሉ፡፡
ወረሐ ሐምሌ ሲሰናበት፣ ወረሐ ነሐሴ ሲያብት ጾመ ፍልሰታ ትጾማለች፡፡ ጾመ ፍልሰታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን “ጾመ ማርያም” እየተባለች ትጠራለች፡፡ ስለ ምን ቢሉ እናታችን የሚሏት፣ አማልጅን እያሉ በሰርክ የሚማጸኗት ቅድስት ድንግል ማርያምን አብዝተው የሚያስቡባት፣ ሐዋርያት እርሷን ለማየት የጾሟት፣ ስለ እርሷም ታሪክ በስፋት የሚነግሩባት ናትና፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየረር መካነ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባኤያት የመጻሕፍት መምህር መላከ ታቦር ኃይለኢየሱስ ፈንታሁን በቤተ ክርስቲያን በአዋጅ የሚታዘዙ ሰባት አጽዋማት አሉ፤ እነዚህን አጽዋማትም ከሰባት ዓመት በላይ ያለ ሁሉ እንዲጾም ይታዘዛል ይላሉ፡፡ ጾመ ፍልሰታ ለምን ተለየች ያሉ እንደኾነ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ የምትወደደው ድንግል ማርያም ናት፡፡ ከኢትዮጵያውያን አንጻር ደግሞ ድንግል ማርያም የተለየ ፍቅር እና ታሪክ አላት ነው የሚሉት፡፡
ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ለማርያም የተለየ ፍቅር እና አክብሮት አላቸው፡፡ በታሪክም እግዚአብሔር ሀገሯን ርስት፣ ሕዝቧን አስራት አድርጎ የሰጣት ለማርያም ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የማርያምን ፍቅር በትውልድ ልብ ላይ ሲጽፉ ኖረዋል፡፡ ከሕጻናት እስከ አረጋውያን ድረስ ለማርያም ልዩ ፍቅር አለ፡፡ ካለው ፍቅር የተነሳ ለጾመ ፍልሰታ ልዩ ጉጉት እና ፍቅር አለ ይላሉ፡፡
ልጅ እያለሁ ይላሉ መላከ ታቦር ስለ ጾመ ፍልሰታ ሲናገሩ በጾመ ፍልሰታ እንኳን ጾም የሚያስፈታ ምግብ ልንበላ ይቅር እና የምግቡን ስም ከጠራን እንቀጣ ነበር፡፡ የፍስክ ምግቦችን የጠራ ሕጻን በሁለት ጠጠር ተጣብቆ ጀሮውን ይቆነጠጣል፤ በሳማም እግሩን ይለበለባል፤ ምግብም ይቀጣል፤ ይሄን የሚያደርጉት ራሳቸው ሕጻናት ናቸው ነው የሚሉት፡፡ ይህ ዝም ብሎ ተራ ነገር አይደለም፣ ምግባር እና ሕግ መማሪያ ነው እንጂ ይላሉ፡፡
በጾመ ፍልሰታ ሕጻናት ወደ ቤተክርስቲያን ይመጣሉ፣ ውሏቸው በቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ ነው፡፡ በዚያም ሃይማኖትን፣ ምግባርን፣ ታሪክን፣ የሀገር ፍቅርን ይማራሉ፡፡ ሕጻናት ንፁሐን ናቸውና በለጋ እድሜያቸው የተማሩትን መልካም ምግባር እና የሀገር ፍቅር ይዘውት ያድጋሉ፡፡ ባደጉም ጊዜ ለሀገር ታላቅ ነገርን ያደርጋሉ፡፡ ልጆች በጾመ ፍልሰታ የሚማሩት ስለ ድንግል ማርያም ነው፡፡ ድንግል ማርያም ደግሞ አዛኝ ናት፣ ስለ አዛኝነቷ ሲማሩ ለሰዎች ያዝናሉ፣ እጅግ ትሑት ናት፣ ስለ ትሕትናዋ ሲማሩ ትሕትና ይኖራቸዋል ነው የሚሉት መላከ ታቦር፡፡
ፍልሰታ ድንግል ማርያም ከመቃብር ተነስታ ወደ ሰማይ የሄደችበት የምትታሰብበት ጾም ናት፡፡ መምህሩ ስለ ታሪኩ ሲናገሩ ድንግል ማርያም በጥር 21 ቀን ባረፈች ጊዜ ሐዋርያት የመምህራቸው፣ የፈጣሪያቸው፣ የአምላካቸው እናት፣ እመቤታቸውን በሥርዓት ሊቀብሯት ይዘው ሄዱ፡፡ አይሁድ ግን ቀድሞ ልጇ ተነሳ፣ አረገ እያሉ እያስተማሩ ዓለሙን ሁሉ ሲያውኩት ይኖራሉ፤ ዛሬ ደግሞ እናቱን ተነሳች አረገች እያሉ ዓለሙን ሲያውኩ ሊኖሩ አይደለምን? እንዲያውም በእሳት ነው የምናቃጥላት ሲሉ በቅናት ተነሱ፡፡ ከእነዚያም ሰዎች መካከል አንደኛው ተራምዶ ሄዶ የአልጋውን ሸንኮር ያዘው፡፡ የእግዚአብሔር መላዕክም በረቂቅ ሰይፍ እጁን ቆረጠው፡፡
ሐዋርያትም ደነገጡ፡፡ ሸሹም፡፡ አስቀድሞ ገና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያልተለየው ዮሐንስ ግን አልሄደም ነበር፡፡ በዚያም ጊዜ የእግዚአብሔር መላዕክ ማርያምን ከዮሐንስ ጋር በደመና ነጥቆ በገነት ከእጸ ሕይዎት ስር አስቀመጣት፡፡ ዮሐንስም ተመልሶ ወደ ሐዋርያት መጣ፡፡ በዚያም ጊዜ ሐዋርያት የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ? አሉት፡፡ እርሱም እመቤታችንማ በገነት ከእፀ ሕይዎት ሥር አለች አላቸው፡፡ እነርሱም እርሱ አይቶ እንዴት እኛ ሳናይ እንቀራለን ብለው እርሷን ያዩ ዘንድ ጾም ለመጾም ወደዱ፡፡
በዚያ ጊዜ የዐቢይ ጾም እየጾሙ ነበርና የዐቢይ ጾም እስኪያልፍ ጠበቁ፡፡ ከጾም ላይ ጾም የለምና፡፡ ጾሙ እንደተፈታም በዓለ ሐምሳ ደረሰ፡፡ በበዓለ ሐምሳም ጾም አይጾምም፡፡ በዓለ ሐምሳ እንዳለቀም የሐዋርያት ጾም የሚባለው ጾም ይገባል፡፡ ጾሙ ሲፈታም በሐምሌ 5 ቀን ሐዋርያት ጉባኤ አደረጉ፡፡ በጉባኤያቸውም ጾሙን መቼ እንጀምር ብለው ተስማሙ፡፡ በነሐሴ አንድ ቀንም ሱባኤ ጀመሩ፡፡ ሱባኤ በገቡ በ14ኛው ቀንም ከገነት እፀ ሕይወት ሥር ያረፈችውን የማርያምን አስከሬን አምጥቶ ሰጣቸው፡፡ ሐዋርያትም ተቀብለው በሥርዓት ቀበሯት፡፡
በዚህ ጊዜ ሐዋርያው ቶማስ አልነበረም፡፡ ቶማስም ከሀገረ ስብከቱ ተነስቶ በደመና ሲመጣ ድንግል ማርያም ስታርግ አገኛት፡፡ ባገኛትም ጊዜ ቀድሞ የልጅሽን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ፡፡ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ አዘነ፡፡ ማርያምም እነርሱ የኔን ትንሳዬ አላዩም፡፡ አንተ ግን አይተሃል ብላ ለምስክር ይኾው ዘንድ ተገንዛ የነበረችበትን ሰበኑን ሰጠችው፡፡ ቶማስም ወደ ሐዋርያት ዘንድ ሄደ፡፡
በደረስም ጊዜ የእመቤታችን ነገር እንዴት ኾነ? አላቸው፡፡ እርሷንም አምጥቶ ሰጥቶን ቀበርናት አሉት፡፡ ቶማስም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይኾናል? አላቸው፡፡ ዛሬም ትጠራጠራለህን? አሉት፡፡ እርሱም አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንማ ተነስታ አረገች አላቸው፡፡ ሐዋርያትም መቃብሩን ሊያዩ ገሰገሱ፡፡ ባዩትም ጊዜ የማርያም ስጋ በመቃብር አልነበረችም፡፡ እነርሱም ቶማስ ትንሳኤዋን እና እርገቷን አይቶ እንዴት እኛ ሳናይ እንቀራለን ብለው በዓመቱ ከነሐሴ አንድ ጀምረው ሱባኤ ያዙ፡፡ በ16ኛው ቀንም ማርያም ራሷ መጥታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ካህን ቀድሶ አቆረባቸው ይላሉ፡፡
በጾመ ፍልሰታ ሕጻናት በቤተ ክርስቲያን ተሠባሥበው ሲጠሯቸው አቤት፣ ሲልኳቸው ወዴት እያሉ ይታዘዛሉ፡፡ የሕጻናት ቁመነገረኛነት፣ ጭምትነት የሚደንቅ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለሕጻናት ምግባርን ታስተምራለች፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማርያም ይታዘዛት፤ እንጨት ይለቅምላት፣ ውኃ ይቀዳላት ነበር፡፡ ሕጻናትም መታዘዝን ይማራሉ፡፡ መምህሩ እንደሚሉት ጾመ ፍልሰታ ሕጻናትን ምግባር፣ ሃይማኖት እና የሀገር ፍቅር ለማስተማር የተመቸች ናት፡፡
ሕጻናት ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩ፣ መልካም ነገር እንዲሠሩ በጾመ ፍልሰታ ይማራሉ፡፡ ወላጆቹን ያከበረ ሀገር ያከብራል፣ ለወላጅ የተመቸ ለሀገርም የተመቸ ነው፤ ወላጆቹን የናቀ እና ያዋረደ ግን ሀገርንም ያዋርዳል ነው የሚሉት፡፡ ሕጻናት ትዕዛዛቱን እየጠቀሱ ሲያስተምሯቸው ምግባር ይማራሉ፡፡ እናት አባትክን አክብር ይባላሉ፤ እናት አባታቸውን ያከብራሉ፡፡ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፣ የባልንጀራህን ገንዘብ አትመኝ ሲባሉ የሰው ገንዘብ እንዳይመኙ ይኾናሉ፡፡ ሰውንም እንደ ራሳቸው ይወድዳሉ፡፡ ሲወዱም ፍቅር ይመጣል፡፡ ፍቅርም ሲኖር ሀገር ሰላም ትኾናለች፡፡ አትግደል፣ አትስረቅ የሚለውንም ሲማሩ ከእነዚህ እኩይ ተግባራት ርቀው፣ እኩይ ተግባራቱንም ንቀው እና ጠልተው ያድጋሉ፤ ይሄን ሲያደርጉም ሀገርን በታማኝነት ያገለግላሉ፤ ከመገዳደል እና ጥላቻ ይርቃሉ ይላሉ መምህሩ፡፡
አሁን በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር መነሻ የምግባር መበላሸት መኾኑን አንስተዋል፡፡ ቤተክርስቲያን ምግባርን የምታስተምር፣ የሀገር ፍቅርን የምታጸና፣ ስለ ሀገር አንድነት እና ሰላም የምትጸልይ ናት ይሏታል፡፡ አቤቱ ሰላምህን ለሀገር ስጣት፣ ጠላቶቿን ከእግሯ በታች አስገዛላት፣ የኢትዮጵያን ሕዝቧን ጠብቅላት እያለች ትጸልያለች፡፡ ይህ ጸሎቷ ዛሬም ሁልጊዜም ያለ ነው ይላሉ፡፡
ያልተገራ ፈረስ እና በሥርዓት ያላደገ ትውልድ አደገኛ ነው፤ ያልተገራ ፈረስ ጌታውን ይሰብራል፤ በሥነ ምግባር ታንጾ ያላደገ ትውልድም ሀገር ያፈርሳል ነው ያሉት፡፡ ሀገር ትጸና ዘንድ ለትውልዱ ምግባርን መሥራት ማስተማር የተገባች ናት ብለዋል፡፡ እንግዲያውስ ስለ ሀገር መልካም ነገርን አድርጉ፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!