ጤና ሚኒስቴር ከ 20 ሚሊዮን ብር በላይ የዓይነት እና ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

13

ባሕር ዳር: ነሐሴ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጤና ሚኒስቴር በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ 20 ሚሊዮን ብር በላይ የዓይነት እና ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የተመራ ከጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የተውጣጣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን አደጋዉ በደረሰበት አከባቢ በመገኘት የተጎጂ ቤተሰቦች፣ ዘመዶች እና ተፈናቃይ ወገኖችን በመጎብኘት አጽናንተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከጉብኝቱ በኋላ በጎፋ ዞን አሥተዳደር በመገኘት ለተጎዱ ወገኖች የተሠባሠበዉን ከ15 ሚሊዮን ብር በለይ የሚገመት የሕክምና ግብአቶች እና ቁሳቁስ እንዲሁም በጥሬ ገንዘብ 5 ሚሊዮን 4 መቶ ብር ለዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ኢንጅነር ዳግማዊ አየለ አስረክበዋል።

ጤና ሚኒስቴር ችግሩ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ተጠሪ ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ አጋር ድርጅቶች እና የግሉን ሴክተር በማስተባበር፣ ባለሙያዎችን እና የሕክምና ግብዓቶችን በመላክ፣ አስፈላጊዉን ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። የሥነ ልቦና ምክር እና ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን የገለጹት ሚኒስትሯ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቀጣይም ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመኾን በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ የድርሻዉን እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውንም የጤና ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ባጋራው መረጃ አስነብቧል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleገቢን በመሰብሰብ ረገድ የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መኾኑን የገቢዎች ሚኒስትር አስታወቀ።
Next article“ፍልሰታ ሕጻናቱ የሚናፍቋት፤ በጉጉት የሚጠብቋት”