
አዲስ አበባ: ነሐሴ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የ2024ቱን ዓለም አቀፍ የክህሎት ውድድርን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ አባል ሀገር ኹና መመረጧ በክህሎት ምህዳሩ ውስጥ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ሚኒስትሯ እንደሀገር ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን ይዞ እንደሚመጣም አንስተዋል። አባልነቱ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የወጣት ኀይል ተጠቅማ ዓለም የደረሰበትን የክህሎት እና የዕውቀት ሽግግርን በዓለም ዙሪያ ማግኘት ያስችላታልም ብለዋል። ኢትዮጵያ አባል የኾነችበት የ2024ቱ ዓለም አቀፍ የክህሎት ውድድር በየሁለት ዓመቱ እንደሚካሄድ ነው የተገለጸው።
ለመጀመሪያ ጊዜም ዘንድሮ በሦስት ዘርፎች ተሳታፊ ትኾናለችም ተብሏል። በቀጣይም ከሚገኘው ልምድ በመነሳት ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት ማቀዷም በመግለጫው ላይ ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!