የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱ መፈተሽ እንዳለበት ተጠቆመ።

10

ባሕር ዳር: ነሐሴ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

በዘንድሮው መውጫ ፈተና ያስፈተኑ 22 የግል ኮሌጆች አንድም ተማሪ አለማሳለፋቸው አነጋጋሪ ኾኖ ቀጥሎል፡፡ የዘርፉ ምሁራን እና ኅላፊዎች ይህ ጉዳይ አሳሳቢ ስለመኾኑ ይናገራሉ። የተለያዩ የመፍትሔ ሀሳቦችንም ይሰጣሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የኾኑት በላይ ሐጎስ (ዶ.ር) እንደሚገልጹት ተማሪዎች ኮሌጅ የሚደርሱት ከታችኛው የትምህርት ክፍል ወጥተው በመኾኑ የመጡበትን መንገድ ምን እንደሚመስል መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡

የትምህርት ሥርዓቱ ተማሪዎች ከክፍል ወደሚቀጥለው ክፍል እንዲሸጋገሩ የሚያበረታታ መኾኑን አንስተው፤ ተማሪዎችን ከክፍል ወደ ክፍል ለማሸጋገር ትኩረት የተሰጠውን ያክል ለእውቀት እና ክህሎት የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መኾኑን ይገልጻሉ፡፡ በተቋማቱ ተማሪዎች እንዳይቀሩ፣ እንዳይደግሙ ትልቅ ቁጥጥር የሚደረግ ቢኾንም ተማሪዎች በቂ የኾነ ዕውቀት እና ክህሎት እንዲያገኙ አስፈላጊው ትኩረት አይሰጥም ይላሉ፡፡

በመኾኑም ይህን ሂደት አልፈው ወደ ኮሌጅ የሚመጡ ተማሪዎች በሚሰጣቸው ፈተና ጥሩ ውጤት ማምጣት አለመቻላቸው ሊደንቀን አይገባም ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ቅድሚያ ትኩረት በሚያስፈልጋቸው የታችኛው ክፍል ተማሪዎች ላይ አልተሠራም የሚሉት በላይ (ዶ.ር)፤ ተማሪዎች ለመማር የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ ብቃት መያዝ አለመያዛቸውን እየለኩ ማብቃት የሚያስችል ሥርዓት አለመዘርጋቱን ይናገራሉ፡፡

እንደ በላይ (ዶ.ር) ገለጻ፤ የትምህርት ሥርዓቱ ካልተስተካከለ በስተቀር የመውጫ ፈተና እየተሰጠ ቢሄድም አሁን የሚታየው ውጤት እየቀጠለ ይሄዳል፡፡ መንግሥት የትምህርት ሥርዓቱን የመቀየር ሂደት በማጠናከር የመሪነት ሚናውን ሊወጣ ይገባዋል፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቢገነቡም እንኳን ከታች ክፍል ጀምሮ ካልተሠራ ውጤታማ መኾን እንደሚከብድ የሚገልጹት በላይ (ዶ.ር)፣ የትምህርት ፋይናንሱ ትኩረት ማድረግ ያለበት በታኛው የትምህርት ደረጃ ነውም ይላሉ፡፡

በመውጫ ፈተናው 22 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምንም ተማሪ አለማሳለፋቸው ጥናት ሊደረግበት የሚገባና ችግር መኖሩን የሚያመላክት ነው የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ትምህርት መምህር ካሣ ሚካኤል (ዶ.ር) ናቸው፡፡ የትምህርት ጥራት ችግር የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቻ አይደለም የሚሉት መምህሩ፤ እንደ ሀገር የትምህርት ጥራት ችግሮችን ለመቅረፍ መሠራት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡

በተጨማሪም መንግሥት እና የግል ተቋማት የትብብር መስተጋብር በመፍጠር ግንኙነታቸው በአሠራር ሥርዓት የተሟላ እንዲኾን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያብራራሉ፡፡ በትምህርት እና ሥልጠና ባለሥልጣን የከፍተኛ ትምህርት ፍቃድ አሰጣጥ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሕይወት አሰፋ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያስመርቋቸውን ተማሪዎች ብቁ ማድረግ እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡

የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ከሚያስፈትኗቸው ተመራቂዎች መካከል ቢያንስ 25 በመቶውን ማሳለፍ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ያብራራሉ፡፡ በሂደት እየሠሩ ቢያንስ 50 በመቶ ማሳለፍ የሚችሉበት አቅም ላይ መድረስ ያለባቸው በመኾኑ ይህ እንዲኾን አዲስ መመሪያ ተግባራዊ ይደረጋል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ዜጎች ትክክለኛ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መርጠው እንዲገቡ የሚያስችል እና ተቋማቱም ተመራጭ የሚኾኑበት የአሠራር ሥርዓት እንደሚዘረጋ የሚያነሱት ወይዘሮ ፍሬሕይወት፤ በቅርቡ ተግባራዊ የሚደረገው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዳግም ምዝገባ ተቋማቱም የትምህርት ጥራትን በማምጣት ተወዳዳሪ እንዲኾኑ በር ከፋች እንደሚኾን ይገልጻሉ፡፡

ተቋማቱ በሚሰጡት የትምህርት ጥራት መሠረት ተመዝነው የሚመዘገቡ እና እውቅ እና ፈቃድ እንደሚሰጣቸው ጠቅሰው፤ ዘርፉ ለትርፍ የሚሠራ ሳይኾን ለሀገር ብቁ ዜጋ ለማፍራት የሚሠራበት በመኾኑ ተቋማቱ ከዓመታዊ ትርፋቸው 25 በመቶውን ለአቅም ግንባታ ማዋል እንዳለባቸው መናገራቸውን ኢትዮጵያ ፕሬስ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበተያዘው በጀት ዓመት የመንግሥት ገቢን ማሳደግ ላይ ዋነኛ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ አሕመድ ሺዴ ገለጹ።
Next article“በተለያዩ ምርቶች እና ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ እና ምርት በደበቁ 66 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል” የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር