
ባሕር ዳር: ነሐሴ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ያለ አግባብ ዋጋ በጨመሩ እና ምርት በደበቁ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መኾኑን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ አስታውቋል። የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኅላፊ ዮናስ መላኩ የማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ማሻሻያ መደረጉ እንደ ሀገር ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ መኾኑን ገልጸዋል።
መምሪያ ኅላፊው አያይዘውም ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተ ለ1 ሺህ 994 ነጋዴዎች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። በ1 ሺህ 552 ነጋዴዎች ላይ በድርጅቶቻቸው ጭምር በመገኘት የበር ለበር ክትትል መካሄዱን ገልጸዋል። በምልከታውም አብዛኛው ነጋዴ ታማኝ እና ምስጉን ኾነው አገኝተናቸዋል ያሉት አቶ ዮናስ መላኩ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ምርት የደበቁ እና ዋጋን ያለ አግባብ በጨመሩ 223 ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱንም አብራርተዋል።
እርምጃ ከተወሰደባቸው ነጋዴዎች መካከል 100 ነጋዴዎች ላይ የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ እና 123ቱ ላይ ደግሞ ድርጅቶቻቸውን እስከ ማሽግ የሚድርስ እርምጃ መወሰዱን መምሪያ ኅላፊው ገልጸዋል። በብዛት ምርት መደበቅ እና የዋጋ ጭምሬ እየታየ ያለው በዘይት ምርት አቅርቦት ላይ በመኾኑ ከተማ አሥተዳደሩ በቂ ዝግጅት እና ክትትል እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
የተጀመረው ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ማኀበረሰቡም ያለ አግባብ ዋጋ በሚጨምሩ እና ምርት በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ ጥቆማ እንዲሰጥ መምሪያ ኅላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!