
ባሕር ዳር: ነሐሴ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ስም በተከፈተ የፌስቡክ አካውንት እየተላለፈ ያለው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ በእንግሊዘኛ የተከበሩ መላኩ አለበል (H.E Melaku Alebel) በሚል ስም በተከፈተ ሐሰተኛ የፌስቡክ አካውንት የሚኒስትሩ ያልሆኑ ሐሳቦች እየተላለፉ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
በማስታወቂያ ክፍያ (በስፖንሰር) ብዙዎች ጋር እንዲደርስ እየተደረገ ባለው በዚህ አካውንት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሥሩ ለሚገኙ አምራች ዘርፎች የገንዘብ ድጋፍ ዕድል ማመቻቸቱን የሚገልጽ ሐሰተኛ መልዕክት ተላልፏል፡፡ መልዕክቱ በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ላይ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ከሚኒስቴሩ የገንዘብ ድጋፍ ዕድል ማግኘት የሚፈልጉ አካላት የተዘጋጀውን የጎግል ፎርም እንዲሞሉ የሚጋብዝ ነው፡፡
በሚኒስትሩ ስም የተላለፈው ሐሰተኛ መልዕክት የገንዘብ ድጋፉ አምራች ዘርፎች ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያላቸውን አበርክቶ ለማሳደግ ያለመ ስለመኾኑ ይናገራል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ ባስተላለፈው መልዕክት በአጭበርባሪዎች በተከፈተ የፌስቡክ አካውንት የተላለፈው መረጃ ሐሰት መሆኑን ጠቅሶ ዜጎች ራሳቸውን ከዘራፊዎች እንዲጠብቁ አሳስቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!