
ባሕር ዳር: ነሐሴ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታውቋል። በጎንደር ከተማ አንዳንድ ነጋዴዎች ያልተገባ ትርፍን ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል ተብሏል። አሚኮ ያነጋገራቸው በጎንደር ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች እንዳሉን አጋጣሚውን በመጠቀም ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ይስተዋላሉ።
ነጋዴዎች ለሀገር እድገት የሚተገበሩ ማሻሻያዎችን ለግል ጥቅም ለማዋል ከመሯሯጥ ተቆጥበው ምርቶችን በተገቢው ዋጋ ማቅረብ እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት። በጎንደር ከተማ በስፋት የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚካሄድበት የአራዳ ክፍለ ከተማ ላይ አንዳንድ ነጋዴዎች ዋጋ ጨምሮ የመሸጥ እና ምርት የመደበቅ ተግባር መፈጸማቸውን የገለጹት የክፍለ ከተማው ንግድ እና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደግፍ ዘውዱ አላግባብ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች ላይም እርምጃ እየተወሰደ መኾኑን አስታውቀዋል።
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በሚገኙ ስድስት ክፍለ ከተሞች ላይ ገበያን የሚቆጣጠር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳድር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ አወቀ ሃጎስ ተናግረዋል። በኀብረተሰቡ ላይ ያልተገባ ጭማሪ ባደረጉ 257 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል። በተጨማሪም በሕገወጥ መንገድ ተከዝኖ የተገኘ 528 ኩንታል ስኳር እና 2 ሺህ 750 ሊትር ዘይት ለመሠረታዊ ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንዲከፋፈል መደረጉን አንስተዋል አቶ አወቀ።
ኀብረተሰቡ ያልተገባ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ሲመለከት የተዘጋጁ የስልክ መስመሮችን በመጠቀም ለሚመለከታቸው አካላት ሊያሳውቅ እና ተባባሪ ሊኾን ይገባልም ተብሏል።
ዘጋቢ: ዳንኤል ወርቄ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!