
ገንዳ ውኃ: ነሐሴ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምዕራብ ጎንደር ዞን የኮሌራ በሽታ ዳግም ማገርሸቱን የዞኑ ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ዮሴፍ ጉርባ ለአሚኮ ገልጸዋል። በሽታው በቋራ እና ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች ከሐምሌ 4/2016 ዓ.ም ጀምሮ መከሰቱን ነው የተናገሩት።
በሽታው ሐምሌ 8/2015 ዓ.ም በቋራ ወረዳ በርሚል ጊዮርጊስ በተባለ የጸበል ቦታ ተከስቶ እንደነበር ያስታወሱት ምክትል መምሪያ ኀላፊው አሁንም በዚህው ጸበል ቦታ ከሐምሌ 11/2016 ዓ.ም ጀምሮ ዳግም ማገርሸቱን ነው ያነሱት።
በተመሳሳይ በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ምድረገነት ከተማ እና ማሀርሽ በተባለ ቀበሌ ከሐምሌ 4/2016 ዓ.ም ጀምሮ ተከስቷል ብለዋል። የበሽታ ሥርጭቱ ከዕለት ዕለት እየተስፋፋ እና የሕሙማን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ጠቅሰዋል።
ምክትል መምሪያ ኀላፊው እንደገለጹት በሽታው ከተከሰተ ጀምሮ እስካሁን ባለው ጊዜ 174 ግለሰቦች በበሽታው ተይዘዋል። በዞኑ የተከሰተው የኮሌራ በሽታ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት እና ሥርጭቱን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር እንዲቻል በዞኑ የክስተት አሥተዳደር ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ጤና መምሪያው ከክልሉ ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች በቂ የመድኃኒት አቅርቦት በማሟላት እና ባለሙያ በማሠማራት የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። እስካሁን በተደረገ የሕክምና እርዳታም ከ137 በላይ የሚኾኑ ሕሙማን ከበሽታው ማገገም ችለዋል።
ይሁን እንጂ በአካባቢው ያለው የጸጥታ ስጋት ተጨማሪ የሕክምና ግብዓት እና ተጨማሪ ባለሙያዎችን ወደ ቦታው ለማጓጓዝ እንቅፋት መኾኑንም ነው አቶ ዮሴፍ ያነሱት። በተመሳሳይ የሕክምና ግብዓቶችን ከጎንደር ገዝቶ ለመምጣትም ጸጥታው ፈታኝ ነው ብለዋል።
በበርሚል ጊዮርጊስ የጸበል ቦታ ብቻ 104 ግለሰቦች በበሽታው መያዛቸውን የጠቆሙት አቶ ዮሴፍ ለመጸበል ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ምዕመናን በሽታው በጸበሉ መከሰቱን አውቀው ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በእርሻ ልማት ጣቢያዎች ያሉ የጉልበት ሠራተኞችን ጨምሮ የዞኑ ማኀበረሰብ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም መምሪያው አሳስቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!