የገበያ ጉድለት በመንግሥት አቅም ብቻ የማይሞላ በመኾኑ የግሉ ዘርፍ ሚና የጎላ መኾኑ ተገለጸ።

16

ባሕር ዳር: ነሐሴ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር ለመሥራት የሚያስችል ውይይት አካሂዷል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በመድረኩ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማሳደግ ወደ ሥራ የገባውን አዲሱን የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ሚና የጎላ መኾኑን ገልፀዋል።

ዘመናዊ እና ተወዳዳሪ የኾነውን ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በመጠቀም የፖሊሲ ማስፈፀሚያ ለማድረግ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ በተለይም በተኪ ምርት፣ የምርት አቅም አጠቃቀም እና እሴት በመጨመር የወጪ ንግድ በማሳደግ ላይ ትኩረት በማድረግ በጋራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የገበያ ጉድለት በመንግሥት አቅም ብቻ የማይሞላ በመኾኑ ሚድሮክ በተጠናከረ መንገድ ገበያውን ለመሙላት መሥራት እንዳለበትም ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ በተለይም በሀገር ውስጥ ተመርተው ለሌሎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚኾኑ ምርቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ኢንዲሰራ በቀጣይ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀማል አሕመድ በበኩላቸ በስሩ ያሉ ድርጅቶችን ከኪሳራ በማዳን የምርት ጥራታቸውን በማሳደግ ሰርቲፋይድ የማድረግ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል፡፡ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ ከመንግሥት ተቋማት ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ሚድሮክ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለውም መግለጻቸውን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የሀገር ውስጥ ምርቶች ተወዳዳሪነታቸው እንዲያድግ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከመንግስት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከሕገወጥ ነጋዴዎች የተወረሰ 800 ሺህ ሊትር ዘይት ተከፋፈለ፡፡
Next articleበዳባት ከተማ የሚገኙት የኢፌድሪ መከላከያ ሠራዊት አባላት የአቅመ ደካሞችን ቤት እየገነቡ ነው።