
ባሕር ዳር: ነሐሴ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከሕገወጥ ነጋዴዎች የተወረሰ 800 ሺህ ሊትር ዘይት ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተከፋፋፍሏል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጉለሌ ክፍለ ከተማ ከሕገ ወጥ ነጋዴዎች የወረሰውን 800 ሺህ ሊትር ዘይት ለ10 የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት አከፋፍሏል።
የፌደራል መንግስት ከሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ተከትሎ ጥቂት ነጋዴዎች መሠረታዊ የፍጆቻ እቃዎች ላይ ሕግ ወጥ ተግባር እየፈፀሙ መኾኑ ተገልጿል።
የክፍለ ከተማው ንግድ መምሪያ ኀላፊ አንዱዓለም ክብረት የምግብ ዘይቱ የተያዘው ሕገወጥ ነጋዴዎች ሰው ሰራሽ እጥረት ለመፍጠር ምርቱን በድብቅ አከማችተው በመገኘቱ ነው ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ ያሻሻለቸውን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊስን ተከትሎ ሕገወጥ ተግባር በሚፈጽሙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መኾኑን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ መንግሥት ያለ ምንም ምክንያት ዋጋ በመጨመር፣ ምርት በመደበቅ እና በመሰወር ሕዝብን በሚያማርሩ አካላት ላይ የተጠናቀረ እርምጃ እንደሚወስድም ገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሕግ አስፈጻሚ አካላት የለውጥ ሥራውን ባልተገባ ሕገ ወጥ መንገድ ለመጠቀም በሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ እንዲወስዱ ኀፊነት ተሰጥቷቸዋል ማለታቸውም ይታወሳል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!