“የብዙ እናቶችን ልብ የሰበረው የሰላም አጦት”

20

ባሕር ዳር: ነሐሴ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተከሰተው የጸጥታ ችግር ወንድም ወንድሙን እና እህቱን እያጠፋ ብሎም አንጡራ ሃብቱን እያወደመ በመኾኑ ተፋላሚ ኀይሎች ልዩነታቸውን በሰላም እንዲፈቱ እናቶች እየጠየቁ ነው። ሀሳባቸውን የሰጡን በጭስ ዓባይ ዙሪያ ነዋሪ የኾኑ እናት ልጃቸው ታጣቂ ኀይሉን ተቀላቅሎ ከመንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ በመግባት ውድ ሕይዎቱን ማጣቱን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሚሊሻ አባል ከመንግሥት ጎን በመኾን የልጃቸው ባል መሰዋቱን ገልጸዋል። “ግጭቱ ወንድም ወንድሙን እና እህቱን እያጠፋ እንዲሁም ሃብት ንብረቱን እያወደመ መኾኑን ሌሎች በግጭት ውስጥ ያሉ አካባቢዎች ከእኛ ቤተሰብ አስከፊ ታሪክ ሊማሩ ይገባቸዋል” ነው ያሉት።

ከጦርነት የሚገኝ ጥቅም ባለመኖሩም ሁሉም ለሰላም መስፈን በቁርጠኝነት መሥራት ይገባዋል ሲሉ ወይዘሮ አብራርተዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪ የኾኑት ወይዘሮ ደግሞ በአካባቢያቸው ጫካ የገቡ ታጣቂዎች በከፈቱት ጦርነት ጸጥታ በማስከበር ላይ የነበረ የፖሊስ አባል ወንድማቸው መሰዋቱን ያነሳሉ።

በተቃራኒው ጫካ የመሸጉ የአጎት እና የአክስት ልጆቻቸው መሞታቸውን ጠቁመው፤ ልክ እንደ እነ እርሱ ቤተሰብ ሁሉ ሌሎች በርካታ ተመሳሳይ አስከፊ የመጠፋፋት ታሪኮች በተለያዩ አካባቢዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። “ወገን ወገኑን አጥፍቶ ለሕዝብ እና ሀገር የሚመጣ በጎ ነገር ስለማይኖር በተለይ እናቶች በየቤታችን ሰላምን ለማስፈን አምርረን መምከር ይኖርብናል፤ የሚገድለውም የሚሞተውም ሰው፤ የሚወድመውም ሃብት የራሳችን ነውና” ብለዋል ወይዘሮዋ።

ሌላኛዋ ሀሳብ ሰጭ የሰሜን ጎጃም ነዋሪ ናቸው። በአካባቢያቸው ሰላም በመጥፋቱ ሠርተው መግባት፣ ነግደው ማትረፍ፣ ልጆቻቸውን ማስተማርም አልቻሉም። በመኾኑም መሣሪያ ታጥቀው ጫካ የገቡ እና መንግሥት ወደ ሰላም ቢመጡ ተጠቃሚው ሕዝብ እና ሀገር ነው ይላሉ። ወይዘሮዋ “ሰላምን ለማስፈን ከራስ ቤተሰብ ይጀምራልና ከቤተሰቦቻችን፣ ከጎረቤቶቻችን እና ከማኀበረሰቡ ጋር ስለሰላም ጠቀሜታ መወያዬት ይገባናል” በማለት ገልጸዋል። የቀረበውን የሰላም ጥሪም ‘ተገቢ ነው’ ሲሉ አወድሰውታል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ለሰላም መስፈን ትልቁን ድርሻ መወጣት ያለባቸው ሴቶች ናቸው ብለዋል። “ሴቶች ባሎቻቸውን፣ ልጆቻቸውን እንዲሁም ወንድሞቻቸውን መምከር እና መመለስ ይገባቸዋ” ነው ያሉት። ቢሮ ኀላፊዋ እንዳሉት ወደ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚኾኑ ሴቶችን በሰላም ዙሪያ ለማወያየት ዕቅድ ተይዟል።

ከሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ባገኜነው መረጃ መሠረት ከክልሉ ሕዝብ መካከል ከ23 ሚሊዮን በላይ የሚኾነው በቀረበው የሰላም ጥሪ ርእሰ ጉዳይ ተወያይቶ አውንታዊ ምላሽ ተገኝቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል 350 ሺህ ሄክታር መሬት ቡናን ለመልማት የተመቼ መኾኑ ተገለጸ።
Next article“እየተከልን እናንብብ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)