
ባሕር ዳር: ነሐሴ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሐምሌ/2016 ዓ.ም የሠለጠነ የሰው ኀይል ወደ አውሮፓ ሀገራት መላክ መጀመሩን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሯ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ዕቅድ አፈፃፀም ተገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተገኙ ልምዶችን በመውሰድ በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሁሉም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እየሠሩ ስለመኾኑ ነው የተናገሩት። የሠለጠነ እና በከፊል የሠለጠነ የሰው ኀይል ቀደም ሲል ከነበረው የመካከለኛው ምሥራቅ መዳረሻ በተጨማሪ ወደ አውሮፓ ሀገራት መላክ መጀመሩ በወሩ ከተመዘገቡ ውጤታማ ሥራዎች ውስጥ መኾኑን ነው ሚኒስትሯ ያብራሩት፡፡
ስምሪቱ የዜጎችን መብት እና ደኅንነት ያስጠበቀ እንዲኾን በማድረግ በሐምሌ/2016 ዓ.ም 26 ሺህ 195 ዜጎችን አሠልጥኖ ለሥራ ማሰማራት መቻሉም ነው የተገለጸው። የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከር በባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን ቅንጅታዊ ሥራ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የሥራ ገበያው የሚያመጣውን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም የማሠልጠኛ ተቋሞችን በአግባቡ አደራጅቶ ጥራት ያለው ሥልጠና እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባም መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡ ሚኒስትሯ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው በዚህ ሥራ ላይ እየተሳተፉ ያሉ አስፈጻሚ እና ባለድርሻ አካላትን አመሥግነዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!