“ምክንያት አልባው የዋጋ ጭማሪ”

57

ባሕር ዳር: ነሐሴ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ አብርሃም ይበልጣል ይባላሉ፡፡ የባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 16 ነዋሪ ናቸው፡፡ ለቤታቸው አስቤዛ ለመግዛት ገበያ ሲዘዋወሩ ነው ያገኘናቸው። ቀይ ሽንኩርት ለመግዛት ነው የመጣሁት ያሉት አቶ አብርሃም አንድ ኪሎ አርባ ብር ሲሸጥ የነበረው ቀይ ሽንኩርት አሁን ሰማንያ ብር እየተሸጠ እንደኾነ ነግረውናል። በእጥፍ ይጨምራል ብየ አላሰብኩም ይላሉ አቶ አብርሃም፡፡

ሌላው ያነጋገርናቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ አቶ አምሀ እየሱስ የሆቴል ቤት ባለቤት ናቸው። አቶ አምሀ 3 ሺህ 1 መቶ ብር እገዛ የነበረው ሃያ ሊትር ዘይት 4 ሺህ ብር ገብቷል ብለዋል። በተጨማሪም 1 መቶ 80 ብር የነበረውን አንድ ኪሎ ነጭ ሽንኩርት 2 መቶ 80 ብር እንደገዙ እና ሁሉም ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳለም ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ጋር በተገናኘ ያናገርናቸው ነጋዴ ዳሳሽ አመራ ሽንኩርት እና ድንችን ጨምሮ የተለያዩ የጥራጥሬ እህሎችንም ሲሸጡ ነው ያገኘናቸው፡፡ ወይዘሮ ዳሳሽ 1 መቶ 60 ብር የነበረ 1 ኪሎ ምስር ክክ1መቶ 90 ብር እየሸጡ ነው ያገኘናቸው፡፡ እንዴት ይህን ያክል ጭማሪ አደረጉ ብለን ላነሳንላቸዉ ጥያቄ በፊት ይገዙበት ከነበረው ዋጋ ላይ ጨምረዉ ስላመጡት እንደኾነ ይገልጻሉ። ወይዘሮ ዳሳሽ አክለዉም እያንዳንዱ ለገበያ የሚያቀርቡት ጥራጥሬ እና አትክልት ዋጋ መግዣ እንደጨመረባቸዉ ተናግረዋል፡፡

ሌላው ያነጋገርናቸው የችርቻሮ ነግዴ አቶ ምግባሩ ደባልቄ ናቸው፡፡ ከውጭ ምንዛሬ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ይስተዋላል ይላሉ። ለምን የዋጋ ጭማሪ ማድረግ አስፈለገ? ቢያንስ ከምንዛሬ በፊት ያስገባችሁትን እቃ በነበረዉ ዋጋ ለምን አትሸጡም? ተብሎ ለተነሳዉ ጥያቄ አቶ ምግባሩ ሲመልሱ ገበያው ላይ ለመቆየት የግድ ምንዛሬዉ በሸቀጦች ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ጭማሪ ታሳቢ አድርገዉ እየሸጡ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

በዚህ መንገድ ካልሸጡ ዋጋ ጨምሮ የሚመጣዉን ምርት ገዝተዉ የማቅረብ አቅም ሊኖራቸዉ እንደማይችል እና ከገበያ ዉጭ ሊኾኑ እንደሚችሉ ነው የተናገሩት፡፡ የክልሉ የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የግብይት ዘርፍ ምክትል ኅላፊ ብዙአለም ግዛቸው የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት ማሻሻያው በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ያብራራሉ። የንግድ ሥርዓቱን በፍትሐዊነት እና በውድድር የተመሰረተ ያደርጋል፤ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ይከሰት የነበረውን የሸቀጦች ጉድለት ይከላከላል ብለዋል። ኀላፊው እንዳሉትም የጥቁር ገበያ ንግዱ እንዳይስፋፋ ያደርጋል ብለዋል። በአጠቃላይ ለንግዱ ማኀበረሰብ በርካታ ቋጠሮዎችን የሚፈታ እርምጃ መኾኑንም ነው የተናገሩት።

አቶ ብዙአለም የምንዛሬ ማሻሻያው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ቢኖሩትም ይህንን ተከትሎ በክልሉ የንግድ ሥርዓት ውስጥ አሉታዊ የኾኑ አሠራሮች እንደታዩ ገልጸዋል፡፡ በተለይም ማሻሻያ ከመደረጉ በፊት የተገዙ ወይም የቆዩ ምርቶችን የመከዘን፣ አግባብ ያልኾነ የዋጋ ጭማሪ የማድረግ፣ ምርቱ እያለ የለም የማለት ኹኔታ እንዳለ ኀብረተሰቡ በሚያደርሰዉ ጥቆማ እና ቢሮዉ ለዚሁ ተግባር አደራጅቶ በላከዉ ቡድን የደረሱ መረጃዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

ይህን ለመከላከል የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ከሚመለከታቸዉ አጋር አካላት ጋር በመተባበር ቡድን በማቋቋም በሪጅዮፖሊታንት ከተሞች እና ዞኖች ላይ ያለዉን የንግድ እንቅስቃሴ መረጃ የመለየት፣ የማስተማር እና እርምጃ የመውሰድ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በየደረጃው የንግድ ሥርዓቱን ለሚያስከብሩ የተዋቀሩ ግብረ ኃይሎች እና የቴክኒክ ኮሚቴዎች ግንዛቤ በመፍጠር ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

አቶ ብዙአለም ለጅምላ ንግድ ነጋዴዎች፣ ለዩኒየኖች፣ ለሸማች ኀብረት ሥራ ማኀበራት እና በሰፊዉ ምርት አቅራቢ ለኾኑ ድርጅቶች አጫጭር መድረኮችን በማዘጋጀት የግንዛቤ ሥራ እየተሠራ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡ አቶ ብዙአለም አያይዘውም በማይሻሻሉ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እና አሥተዳደራዊ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ ድርሻ ያላቸዉ የተለያዩ የማኀበረሰብ ክፍሎች፣ አደረጃጀቶች እና የመንግሥት መዋቅሮች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸዉ አካላት በሸማቹ ላይ የሚደርሰውን ያልተገባ ጫና እና የኑሮ ውድነት በመቆጣጠር እና ጥቆማ በመስጠት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ የክልሉ የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የግብይት ዘርፍ ምክትል ኅላፊ ብዙአለም ግዛቸው የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያውን ተከትሎ ምክንያታዊ ያልኾነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ኀብረተሰቡ ሊያጋልጥ ይገባል ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቺርቤዋ አምሊ 30/2016 ም.አሜቱ ጋዚቲ
Next article“የኮሪደር ልማት ሥራው ጥራቱን ጠብቆ እየተሠራ ነው” የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ