
ባሕር ዳር: ነሐሴ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደረጉ ላይ የማስተካከያ እርምት እየተወሰደ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገልጿል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተከትሎ ምክንያታዊ ባልኾነ ሁኔታ ከማሻሻያው በፊትም የተገዙ የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ የማስተካከያ እርምት መወሰዱ ነው የተብራራው።
በጎንደር ከተማ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ በንግድ ተቋም ባለሙያዎች እና በተደራጀው ግብረ ኀይል አማካኝነት የተለያዩ እርምቶች እየተወሰዱ መኾኑ ተጠቁሟል። በስድስቱም ክፍለ ከተሞች የግብረ ኀይል ዕቅድ ወርዶ ግንዛቤ በመፍጠር ወደ ሥራ የተገባ ሲኾን ባለፉት ሰባት ቀናት ለ1ሺህ 666 የንግድ ድርጅቶች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተሠርቷል ተብሏል፡፡
ያለ ምንም በቂ ምክንያት ያለ አግባብ ዋጋ ጨምረው የተገኙ 103 የንግድ ድርጅቶች፣ ያለንግድ ፈቃድ ሲነግዱ የተገኙ 154 የንግድ ድርጅቶች፣ መንግሥት ከተመነው ታሪፍ በላይ ዋጋ ጨምረው ሲሸጡ የተገኙ ሁለት የነዳጅ ማደያዎች በጥቅሉ በ258 የንግድ ድርጅቶች ላይ የማሸግ እርምጃ ስለመወሰዱ ነው የተገለጸው፡፡
አንድ የንግድ ድርጅት ባለቤት ለሥራው መተባበር ባለመቻሉ እና ለሕዝብ ለመሸጥ ፈቃደኛ ባለመኾኑ በሕግ እንዲጠየቅ ስለመደረጉም ነው የተብራራው። በከተማው ፍተሻ ከተካሄደባቸው 15 ትላልቅ የምርት መጋዝኖች ውስጥ አምስቱ አላግባብ ከዝነው በመገኘታቸው መታሸጋቸው ተገልጻል፡፡ ተከዝነው ከተገኙ ምርቶች መካከል 528 ኩንታል ስኳር እና 2ሺህ 750 ሊትር ዘይት እንደኾኑም ከተማ አሥተዳደሩ አስገንዝቧል።
3ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት፣ 130 ኩንታል ስኳር እና 20 ኩንታል ሩዝ በቆየው ዋጋ ለኅብረተሰቡ እንዲሰራጩ ስለመደረጉም ነው የተገለጸው፡፡ ከተማ አሥተዳደሩ ገቢያን ለማረጋጋት ለመንግሥት ሠራተኛው በራስ ዳሽን ዩኔየን አማካኝነት በ11ሺህ 500 ብር ጤፍ በሦስት ወር ክፍያ እየተሰራጨ ስለመኾኑም ነው የተብራራው፡፡
400 ኩንታል የዳቦ ዱቄት በ81 ብር ስለመከፋፈሉም ነው የተገለጸው፡፡ በቀጣይም ከፋብሪካዎች ጋር መግባባት ላይ በመደረሱ በቀጣይ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን ለኅብረተሰቡ ማድረሱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመላክቷል። ታሽግው የሚገኙ መጋዝኖች በቀጣይ ተመክረው ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያሰራጩ እንደሚደረግም ነው የተገለጸው።
በንግድ መጋዝኖች እና የችርቻሮ መሸጫዎች ላይ ያልተገባ ጭማሪ ኅብረተሰቡ ሲያጋጥመው በአቅራቢያው ላለ የንግድ እና ገበያ ልማት ተቋም አለያም ለሚመለከተው ግብረ ኀይል ጥቆማ በመስጠት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል የሚሠራውን ሥራ እንዲያግዝም ከተማ አሥተዳደሩ ጠይቋል፡፡
ገቢያን ለማረጋጋትም ከተማ አሥተዳደሩ በቀጣይ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራም ከከተማው ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!