“በምክክር ሂደቱ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት የውጭም ኾነ የውስጥ ጣልቃ ገብነት አልታየም” ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

17

ባሕር ዳር: ነሐሴ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የምክክር ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ስለመኾኑ ተናግረዋል። በአሥር ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተጀመረውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እስከ መስከረም 30/ 2017 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደኾነም አስረድተዋል።

በአማራ እና ትግራይ ክልሎችም አንጻራዊ ሰላም በተገኘበት አጋጣሚ ሁሉ ወደ አጀንዳ ልየታ ለመግባት ዝግጅት መደረጉን ፕሮፌሰር መስፍን አብራርተዋል። በአንዳንድ ቦታዎች ያለው የጸጥታ መደፍረስ ሁኔታ የተወሰነ ተጽዕኖ ቢያሳድርም በተጀመረባቸው ቦታዎች የአጀንዳ ማሰባሰቡ ሂደት በተገቢው ሁኔታ እየሄደ እንደሚገኝም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

የአጀንዳ ልየታው እስከ መስከረም መጨረሻ የገፋው አፋር ክልል በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ሙቀት እየገባ በመኾኑ ነው ብለዋል። የኮሚሽኑ ዋና ተግባር አካታች እና አሳታፊ የኾነ ሀገራዊ ምክክር ማካሄድ በመኾኑ ኮሚሽኑ ለሁሉም ዜጎች የጋራ መድረክ እያመቻቸ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር እየሠራ መኾኑን አስረድተዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን የምክክሩ ዓላማ ከሕዝብ የተሰበሰቡ አጀንዳዎች ሁሉ በሚገባ ተለይተው በተመረጡ የሀገሪቱ ተወካዮች በኩል አስፈላጊውን ውይይት ተደርጎ ከመግባባት መድረስ መኾኑን አንስተዋል። “በምክክር ሂደቱ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት የውጭም ኾነ የውስጥ ጣልቃ ገብነት አልታየም” ብለዋል ፕሮፌሰር መስፍን። ነገር ግን የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉ ወገኖች ወደ ሀገራዊ ምክክሩ አለመምጣታቸው የራሱ የኾነ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛ በመኾኑ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ708 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል መሸፈኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።
Next article“ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ እና ምርትን ባከማቹ 258 የንግድ ድርጅቶች ላይ ሕጋዊ እርምት ተወስዷል” የጎንደር ከተማ አሥተዳደር