
ባሕር ዳር: ነሐሴ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሴቶችን ንጽህና መጠበቂያ በሁሉም አካባቢዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ እና የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት ያለመ የግል እና የመንግሥት ባለድርሻ አካላት የስትሪንግ ኮሚቴ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች ተፈጥሮዊ የኾነውን የወር አበባ የሚያዩበት ሂደት በተዛባ አመለካከት እና የግንዛቤ እጥረት ምክንያት ትኩረት ሲነፈገው ቆይቷል ብለዋል።
“በወር አበባ ዙሪያ በተሠሩ ሥራዎች በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡ ቢኾንም ሰፊ ጥረት የሚሹ ጉዳዮች አሉም” ብለዋል። ዶክተር መቅደስ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች እና አገልግሎቶችን ለሁሉም ሴቶች ተደራሽ ለማድረግ ሁሉም የግል እና የመንግሥት ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት እና በቅንጅት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሴቶች እና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) በበኩላቸው የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ በኮስሞቲክስ እቃዎች ዝርዝር ውስጥ የተካተተ እንደነበር አስታውሰዋል። ከቅንጦት እቃ ዝርዝር መውጣቱ እና 30 በመቶ የነበረው ቀረጥ ወደ 10 በመቶ መውረዱ አበረታች እርምጃ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ኤርጎጌ (ዶ.ር) አክለውም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚታየው የማግለል እና የተዛባ አስተሳሰብን ለማሥቀረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሠሩ ይገባል ማለታቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!