
ባሕር ዳር: ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት አብየ ካሣሁን እና የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ኃይለየሱስ ተስፋማርያም ምሥጋና እና አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል። የአማራ ክልል ምክር ቤት በ6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 8ኛ መደበኛ ጉባኤው የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት ሾሟል።
በሹመቱም አቶ አለምአንተ አግደው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እና አቶ ሙሉዓለም ቢያዝንን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ኾነው መሾማቸው ይታወቃል። በመኾኑም በቀድሞዎቹ እና በአዲሶቹ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንቶች መካከል የሥራ ርክክብ እና የምስጋና ፕሮግራም ተደርጓል።
በሥነ ሥርዓቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት አብየ ካሣሁን እና የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ኃይለየሱስ ተስፋማርያም ምሥጋና እና አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው የተሰጣቸው ኀላፊነት ከባድ እና ከፍተኛ መኾኑን ገልጸው ከፍርድ ቤት መሪዎች፣ ከዳኞች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በከፍተኛ ተነሳሽነትና ትጋት ለመፈጸም ዝግጁ ነኝ ብለዋል። ፍርድ ቤቶች ከሦስቱ የመንግሥት አካላት አንዱ በመኾናቸው በሕገ መንግሥት የተሰጣቸው ተልዕኮ ነጻ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች፣ መሠረታዊ ነጻነቶች እና የንብረት መብትን በማስከበር ለሀገር የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል። የሕግ የበላይነት እና እኩልነት መረጋገጥ ለሁሉም አካል ዋስትና ናቸውም ብለዋል። ፍርድ ቤቶች ዜጎች በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ አቅርበው ነጻ እና ትክክለኛ ዳኝነት የሚጠይቁባቸው ብቸኛ አማራጭ የፍትሕ መድረኮች ናቸው ብለዋል። ዜጎች ነጻና ትክክለኛ የዳኝነት አገልግሎት ከፍርድ ቤቶች የማያገኙ ከኾነ በመንግሥት ቅቡልነት ላይ ጥያቄ የሚያነሱበት እና መብታቸውን ለማግኘት ሌሎች አማራጮችን የሚፈልገለበት ኹኔታ ይፈጥራል ነው ያሉት።
ይህም ለማያባራ ማኅበራዊ ቀውስ እና ለሀገር መቆርቆዝ ይዳርጋል ነው ብለዋል። የሚሰጠው የዳኝነት አገልግሎት ዜጎች በፍርድ ቤቶች ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳድግ መኾን አለበት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ። አቶ ዓለምአንተ ሌሎች ተቀባይነት ያላቸው ሕጋዊ የሙግት መፍቻ አማራጮች እንደተጠበቁ ኾነው ዜጎች አለመግባባታቸውን በሠለጠነ መንገድ በፍርድ ቤት የሚፈቱበት ሁኔታ ባሕል የሚኾንበት ሥርዓት አስፈላጊነትን ጠቅሰዋል።
ፍርድ ቤት ዳኞች የዳኝነት ነጻነት እንደሚያስፈልጋቸው እና ከተሸከሙት ከፍተኛ የሕዝብ ኀላፊነት አኳያ በአማራ ክልል ነጻ የዳኝነት ሥርዓትን ለመገንባት ሁሉም ድርሻ እንዳለበት አመላክተዋል። አማራ ክልል በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሲያገለግሉ ባላቸው አቅም እና የሥራ ጥራት ስመጥር የኾኑ ዳኞች የሚወጡበት ክልል መኾኑንም ጠቅሰዋል። ፕሬዚዳንቱ በክልሉ ውስጥም የዳኝነት ነጻነት የተረጋገጠ መኾኑ የተመሠከረለት ነው ብለዋል። ይህንን መልካም ሥም እና የዳኝነች ነጻነትን አረጋግጦ መቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
መንግሥት ለዳኝነት ሥርዓቱ በቂ በጀት መመደብ የሚጠበቅበት መኾኑ ሌላኛው የዳኝነት ነጻነት መገለጫ ነው ብለዋል። ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔ የበላይ ፍርድ ቤቶች ካልሻሩት በስተቀር አሥፈጻሚውን ጨምሮ በሁሉም አካል መከበር እና መፈጸም ያለበት መኾኑንም አመላክተዋል።
ክርክሮችን በፍትሐዊነት መምራት፣ የተከራካሪዎችን መብት ማክበር እና የተፋጠነ ፍትሕ መስጠት በትኩረት እንደሚሠራበት ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። ክልሉ ካለበት ወቅታዊ ችግር አኳያም በተለየ ትኩረት እቅድ ታቅዶ የፍትሕ መዘግየትን ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የታገዘ ተደራሽ የዳኝነት አገልግሎትን ለማሳደግ እንሠራለን ነው ያሉት።
ዳኞች ነጻ እና ገለልተኛ ኾነው በመሥራት የዳኝነትን ክብር እንዲያስጠብቁ ለማድረግ አንዳንድ የሚታዩ የፍትሕ አሰጣጥ ውስንነቶችን ለማረም ሁሉንም ዳኞች እና ኅብረተሰቡን በማወያየት ተገቢ ማስተካከያ ይደረጋል ነው ያሉት። የዳኞች ምልመላ፣ ሹመት፣ እድገት እና ዝውውር በግልጽ በተቀመጠ ሥርዓት እና በፍትሐዊነት እንዲፈጸም ትኩረት ይሰጣል ብለዋል።
አዲሱ የፍርድ ቤት መሪ የየደረጃው መሪዎችን፣ ዳኞችን እና መላውን ሠራተኞች በማሳተፍ በዳኝነት አገልግሎት ላይ የሚታየውን ችግር ለይቶ ለመፍታት እንሠራለን ብለዋል ፕሬዚዳንቱ። የዳኞቸችን አቅም በመገንባት እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፈጣን፣ ተደራሽ እና ጥራት ያለው የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት እንሠራለን ብለዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ባደረጉት ንግግር ከኀላፊነታቸው የተነሱ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የቀድሞ ፕሬዚዳንቶችን በአስቸጋሪ ጊዜ ፍርድ ቤቱን በመምራት በተሟላ ሥነ ምግባር እና በቀናነት ለሰጡት አገልግሎት አመሥግነዋል። ከኃላፊነታቸው የተነሱት የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንቶች በጥሩ ሥነ ምግባር ፍርድ ቤቱን ሲመሩ መቆየታቸውን የጠቀሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ያገለገለን ሰው አመሥግኖ በክብር የመሸኘትን አስፈላጊነት ገልጸዋል። የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት ለማሻሻል ውይይት ያደረጉባቸውን እና መተጋገዝ የሚያስፈልጉ ዘርፎችም መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
የአስፈጻሚውን ጣልቃ ገብነት የማረም አስፈላጊነት የጠቀሱት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የዳኝነት አካሉ ያለበትን የሥራ ጫና እና የሚጠይቀውን የሥነ ምግባር ጥራት እንደሚረዱም ገልጸዋል። በክልሉ የዳኝነት እና ፍትሕ አሰጣጡ በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት እና ውስብስብ በመኾኑ ዳኞች መደጋገፍ እንደሚያስፈልጋቸው አሳስበዋል። በሀገር ደረጃ የተጀመረው የፍትሕ ማሻሻያንም በመገንዘብ የክልሉን የዳኝነት ሥርዓት በማሻሻል የዜጎችን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መንገድ ቃኝቶ ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ያስፈልጋል ብለዋል።
የክልሉ መሪ የሚቀርብለትን ተናጠላዊ እና ተቋማዊ የትብብር ጥያቄዎች ለማዳመጥ እና ለማገዝ ከጎናችሁ ነው ብለዋል። በሥነ ሥርዓቱ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ እና በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አሥተባባሪ እና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰውን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ባለሥልጣናት፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች እና ሠራተኞች ተገኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!