
ባሕር ዳር: ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ ከቆላድባ-ሮቢት የሚገኘው ጠጠር መንገድ መልሶ ግንባታ የደረጃ ማሻሻያ ሥራ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።
ከቆላድባ -ሮቢት የሚገኘው የጠጠር መንገድ መልሶ ግንባታ 16.5 ኪሎ ሜትር በክልሉ መንግሥት በጀት ድጋፍ በመንገድ ቢሮ ባለቤትነት በከልሉ ገጠር መንገድ ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ የጎንደር ጥገና ጽሕፈት ቤት ሙሉ ሥራው ተሠርቷል።
የተሠራው የጠጠር መንገድ መልሶ ግንባታ ዘጠኝ ቀበሌዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ገበባ ሳልጅ፣ ጉራንባ፣ አረብያ፣ አቸራ፣ ደብርዙሪያ፣ አዲስጌ፣ ጣናወይና፣ ጃርጃር እና ሰራቫ ዳብሎ ቀበሌዎችን ያገናኛል። ከሁሉም በላይ የአካባቢው ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ ጊዜ ይቸገርበት የነበረውን የመንገድ ጥያቄ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መፍታቱን በእጂጉ አመስግነዋል።
በባለፈው ዓመት በመገጭ ወንዝ ላይ 78 ሜትር እግረኛ ተንጠልጣይ ድልድይ በመገንባቱ ሰባት ቀበሌዎች ተጠቃሚ ከማድረጉም በላይ በወንዙ ሲከሰቱ የነበሩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲፈቱ አድርጓል።
በተጨማሪም በ2016 በጀት ዓመት የጠጠር መንገድ መልሶ ግንባታ የጥገና ፕሮጀክት በመሠራቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ የክልሉን መንግሥት ማመስገኑን ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኮሙንኬሽን መምሪያ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!