ለሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊ በተለየባቸው ክልሎች አጀንዳ የመለየት ሥራ እየተከናወነ መኾኑ ተገለጸ።

17

ባሕር ዳር: ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊ እና ቃል አቀባይ ጥበቡ ሰለሞን እንደገለጹት ከአማራ እና ከትግራይ ክልል ውጪ በሌሎች ክልሎች አጀንዳ የማሰባሰቡ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በምክክሩ ያልተካተቱት የአማራ እና የትግራይ ክልሎች እንደ ችግር ቢታይም በጊዜ ሂደት ችግሮች ሲቃለሉ እና አንጻራዊ ሰላም ሲገኝ ሁለቱም ሀገራዊ ምክክሩ ላይ እንደሚሳተፉ እና ወደ ሂደቱ የሚገቡበት ቅንጅታዊ አሠራር እየተሠሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

እስከ አሁን በአዲስ አበባ ደረጃ አጀንዳ ተሰባስቦ ለኮሚሽኑ መቅረቡን ያስታወሱት አቶ ጥበቡ አሁን ላይ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልል አጀንዳ የማሰባሰቡ ሂደት ተጠናቅቆ ለኮሚሽኑ መቅረቡን አመልክተዋል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር እና በሀረሪ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በቀጣይ እንደሚከናወን ጠቅሰው እስከ አሁን የተካሄደው ጉዞ አካታች እና አሳታፊ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

የቅድመ ዝግጅት እና የዝግጅት ሥራዎች በአብዛኛው በአግባቡ መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል። የሂደት ምዕራፍ ላይ በዋናነት በጉዳዩ መግባባት እንዲፈጠር የግንዛቤ ሥራዎች እና ተሳታፊ በተለየባቸው ክልሎች ላይ አጀንዳ የመለየት ሥራ እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ በተለይ ተሳታፊ ባልተለየባቸው የአማራ እና የትግራይ ክልሎች ሂደቱ እንዲቀጥል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አመልክተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቀማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባው የደሴ ዱቄት እና ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ፡፡
Next articleመገናኛ ብዙኃን ለኀብረተሰቡ ወቅታዊ እና የጠራ መረጃ በማድረስ ለሰላም እና ለአብሮነት መጠናከር ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሠሩ ተጠየቀ፡፡