
ደሴ: ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በቀን 300 ሺህ ዳቦ የማምረት አቅም ይዞ በቀማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባው የደሴ ዱቄት እና ዳቦ ፋብሪካ ተመርቋል፡፡ በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ተገኝተዋል፡፡
በምርቃት መርሐ ግብሩ የእንኳን ደኀና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ “ፋብሪካው የሰላም እና አብሮነት ከተማ ለኾነችው ደሴ የተበረከተ ተጨባጭ ስጦታ ነው” ሲሉ አመሥግነዋል፡፡ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽሕፈት ቤት ተገንብቶ ለምርቃት የበቃው ፋብሪካ የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋት በኩል የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እንደ መሪ እና እንደ እናት ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በመላው ሀገሪቱ እያስመረቁ መኾኑን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ እያከናወኑት ስላለው ዘመን ተሻሪ ሥራ በክልሉ መንግሥት ሥም አመሥግነዋል፡፡ በፋብሪካው የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለሰላም ወዳዱ የደሴ ሕዝብ በቀዳማዊት እመቤት የተገነባው የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡
ክብርት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ በርካታ ትምህርት ቤቶችን፣ የዳቦ እና የዱቄት ፋብሪካዎችን በመገንባት ለተግባር እያበቁ መኾናቸው አገልጋይነታቸውን በእጅጉ ያሳያል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። እያከናወኑት ያለው በጎ ተግባርም በየአካባቢው በሕዝብ እና በመንግሥት ከፍተኛ ተቀባይነትን ያስገኘ ነው ብለዋል፡፡
የደሴ ዱቄት እና ዳቦ ፋብሪካን መርቀው የከፈቱት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው “በቀን 300ሺህ ዳቦ እና 150 ኩንታል ዱቄት የማምረት አቅም ያለውን ፋብሪካ በፍቅር እና በሰላም ከተማዋ ደሴ በማስመረቃችን ደስተኞች ነን” ብለዋል፡፡ “የፋብሪካው ተመርቆ ሥራ መጀመር የእኛ ጥረት ብቻ ሳይኾን የከተማዋ ማኅበረሰብ በጎነት ታክሎበት ነው“ ያሉት ቀዳማዊት እመቤቷ “ፋብሪካው የራሳችሁ ሃብት ነውና ጠብቁት” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጀማል ይማም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!