የጎርፍ መጥለቅለቁ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የፎገራ አርሶ አደሮች ጠየቁ።

67

ባሕር ዳር: ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን በፎገራ እና ሊቦ ከምከም ወረዳዎች የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ አጋጥሟል። በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ፣ ሊቦ ከምከም እና ደራ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች የጎርፍ አደጋ ስጋት እንዳለባቸው በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል። ነዋሪዎቹ ከክረምቱ መክበድ ጋር ተያይዞ የጎርፍ መጥለቅለቅ ሊገጥማቸው እንደሚችል እና የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ እንዲሠራም ጠይቀው ነበር።

አስቀድመው በጎርፍ አደጋ ስጋት የነበሩ አርሶ አደሮች ከሰሞኑ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት አካባቢያቸው በጎርፍ ተጥለቅልቆባቸዋል። በፎገራ ወረዳ የአቫ ኮኪት ቀበሌ ነዋሪው አበራ ባንቴ “የገጠመን ጎርፍ ከወትሮው የተለየ ነው” ብለዋል። ትናንት ሌሊት የገጠማቸው የጎርፍ መጥለቅለቅ ከረጅም ዓመታት በኋላ የታየ ከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ እንደኾነ ነው የተናገሩት። መሰል ከባድ የጎርፍ መጠለቅለቅ የገጠማቸው በ1980 ዓ.ም እንደነበር አስታውሰዋል።

ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም ለሐምሌ 30/2016 ዓ.ም አጥቢያ በሌሊት የመጣው የጎርፍ መጥለቅለቅ በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል ብለዋል። የጎርፍ መጥለቅለቁ የገጠመው ሌሊት በመኾኑ ደግሞ ለመከላከል እና ከአደጋው ለመውጣት አስቸጋሪ እንደነበር ነው የተናገሩት። ሰው እንደተኛ የመጣ የጎርፍ መጥለቅለቅ በመኾኑ ከባድ እና አስደንጋጭ እንደነበርም ገልጸዋል።

በጎርፍ ከተጥለቀለቀው ቤታቸው ልጆቻቸውን ለማውጣት ተቸግረው እንደነበርም ተናግረዋል። በጎተራ እና በእህል ማስቀመጫ ኬሻ ያስቀመጡት እህል በጎርፍ መጥለቅለቁ እንደተጎደባቸውም ገልጸዋል። ቤታቸው ለአስፓልት መንገድ ቅርብ በመኾኑ ልጆቻቸውን ማውጣት መቻላቸውን የተናገሩት አቶ አበራ ራቅ ወደአለ አካባቢ ቤታቸው በጎርፍ የተዋጠባቸውን ሰዎች ለማውጣት ግን ጀልባ ያስፈልጋል ብለዋል።

ብዙዎች በራሳቸው ጥረት ከጎርፍ እየወጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ቤታቸውን ግን ለጎርፍ መጥለቅለቅ መልቀቃቸውን ነው የገለጹት። ሊመጣ የሚችለውን የጎርፍ አደጋ አስቀድሞ በማሰብ የጥንቃቄ መልዕክት ተላልፎ እንደነበር እና የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተሠርቶ እንደነበር ነው የተናገሩት። ነገር ግን የጎርፍ ማጥለቅለቁ ከተደረገው ዝግጅት በላይ ነው ብለዋል።

የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል። “ለእንስሳት ያከማቸነው መኖ በጎርፍ ተውጧል፣ ከብቶቻችን ይዘን ወደ ኮረብታማ አካባቢ እንድንሄድ እና ጎርፉ እስኪያልፍ ድረስ በዚያው እንድንቆይ እንዲመቻችልን እንፈልጋለን” ነው ያሉት። የጎርፍ አደጋ ያልገጠማቸው አካባቢዎችም እንስሳትን ይዘው ሲሄዱ እንዲቀበሏቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ ቸሩ መኮንን ያሳለፉት ሌሊት ከባድ እንደነበር ተናግረዋል። ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም ቀን ላይ የመጣው የጎርፍ መጥለቅለቅ በከፊል ነበር፣ ሌሊት የኾነው ግን አስደንጋጭ እና አደገኛ ነው ብለዋል። ቤታቸውን ለቀው መውጣታቸውን የተናገሩት አቶ ቸሩ እህላቸው በጎርፍ ተውጦ መቅረቱንም ገልጸዋል።

ከጎርፍ መጥለቅለቅ ለመውጣት ጀልባ ጠይቀው እንዳልደረሰላቸውም ተናግረዋል። እስካሁን የደረሰልን የለም፣ አሁንም የከፋ ጉዳት እንዳይገጥመን ስጋት ላይ ነን ብለዋል። መንግሥት አስቸኳይ የነፍስ አድን ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በቀጣይ ሁለት ወራት ቅጽበታዊ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት እና የአነስተኛ ግድቦች ከመጠን ያለፈ መሙላት ሊከሰት ይችላል ብሏል።

የክረምት ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ከመደበኛ በላይ የዝናብ ምጣኔ ይጠበቃል ተብሏል። ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን ከሚጥልባቸው አካባቢዎች መካከል ደግሞ አማራ ክልል አንደኛው ነው። የሚጥለው ከመደበኛ በላይ ዝናብ በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቅም ቢኖረውም የመሬት መንሸራተት፣ የአፈር መሸርሸር እና ማሳ ላይ ዉኃ የመተኛት ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ ነው የተባለው። ሊደርስ ከሚችለው ጉዳት ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግም የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳስቧል።

ኢንስቲትዩቱ መግለጫ በሰጠበት ቀን ታዲያ በደቡብ ጎንደር ዞን በፎገራ እና ሊቦ ከምከም ወረዳዎች የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከስቷል። የደቡብ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በላይ አስራደ በወረዳዎች የተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ አስቸጋሪ መኾኑን ገልጸዋል። የገጠመው ችግር ከአካባቢው አቅም በላይ መኾኑንም ተናግረዋል። አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግ አስቀድመው የጠየቁት ድጋፍ ሳይሳካ መቅረቱንም ገልጸዋል። የጎርፍ መከላከያ የሚኾኑ መከተሪያዎች ለመሥራት ያቀረቡት ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ አለመመለሱንም ተናግረዋል። አስቀድመው ያዘጋጇቸው የአደጋ ጊዜ ጀልባዎች ካለው ችግር አንጻር በቂ አይደሉም ነው ያሉት።

በርካታ ወገኖች ቤታቸው በጎርፍ ተውጦ በቆጥ ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል። አርሶ አደሮችን ወደ ተሻለ ቦታ አውጥቶ በጊዜያዊ መጠለያ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ለጊዜያዊ መጠለያ የሚኾን የጠየቁት ድንኳን እንዳልተሰጣቸውም ገልጸዋል። የጸጥታ ችግሩ በፍጥነት ገብተው ድጋፍ ለማድረግ እንዳላስቻለም ተናግረዋል። በጸጥታ ችግሩ ምክንያት አርሶአደሮች ለሚያቀርቡላቸው ጥያቄ መልስ ለመስጠት መቸገራቸውን ተናግረዋል። ድረሱልን የሚሉ ወገኖችን ለማዳን የክልሉ መንግሥት እና የፌዴራል መንግሥት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ዳይሬክተር ብርሃኑ ዘውዱ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የጎርፍ መጥለቅለቅ ችግር ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል። የወንዞችን ዳር መገደብ፣ መከተር እና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን ነው የተናገሩት። የተሠሩት ሥራዎች የጎርፍ መጠኑን እንደሚቀንሱም ገልጸዋል።

ለወረዳዎች ለክትትል እና ለአደጋ መከላከል የሚኾኑ ጀልባዎችን መስጠታቸውንም አንስተዋል። ነገር ግን ጀልባዎችን በአግባቡ ያለመጠቀም ችግር መኖሩን ነው የተናገሩት። ክረምቱ ከበድ ያለ በመኾኑ አሁን ከተፈጠረው የበለጠ ወደፊት ሊከሰት እንደሚችልም ገልጸዋል። በተለይም ከጣና መሙላት ጋር ተያይዞ አደጋ ሊከሰት ይችላል ነው ያሉት። ኮሚሽኑ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየሠራ ነውም ብለዋል።

ጀልባ ወደ ሥፍራው እንደሚላክም ተናግረዋል። ጀልባውን በተገቢው መንገድ መጠቀም እና ማሥተዳደር እንደሚጠይቅም አስረድተዋል። የውኃ ወለድ በሽታዎችን ለመታደግ የሚያስችሉ ድጋፎች መደረጋቸውንም ገልጸዋል። አደጋ የሚቀንሱ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ይሠራልም ብለዋል። ለአካባቢዎቹ የቅድመ ዝግጅት ሥራ የተሻለ ድጋፍ ተደርጓል ነገር ግን ከፍላጎት አንጻር ሙሉ አይኾንም ነው ያሉት። በየወረዳዎች የመጠባበቂያ ድንኳን አለ ያሉት ዳይሬክተሩ ከዚያ ያለፈ ከኾነ ከክልል ይላካል ብለዋል።

በክልሉ የጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት የቅድመ መከላከል ሥራዎች እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ይስተዋላል” የባሕርዳር ነዋሪዎች
Next articleበቀማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባው የደሴ ዱቄት እና ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ፡፡