
ባሕር ዳር: ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከተደረገው የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያ ጋር ተያይዞ የአውሮፕላን ቲኬት ዋጋን በተመለከተ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
የማብራሪያው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
የኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘብ ላይ የተደረገውን የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያ ተከትሎ የኢትዮዽያ አየር መንገድ የዓለም-ዓቀፍ እና የሀገር ውስጥ ጉዞ የአውሮፕላን ቲኬት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል የሚል መረጃ በተለያዩ የበይነ-መረብ የመገናኛ ብዙሃን መሠራጨቱን አስተውለናል። ይህንንም ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ለተከበራቸሁ መንገደኞቻችን የሚከተለውን ማብራሪያ ለመስጠት እንወዳለን።
በዓለም ዓቀፍ የአየር ትራንስፖርት አሠራር የዓለም-አቀፍ ጉዞ የአውሮኘላን ቲኬት ዋጋ የሚተመነው በአሜሪካን ዶላር ወይም በተመሳሳይ ገንዘቦች (Currency) ነው። ይሁን እንጂ መንገደኞች በየሀገሩ ቲኬት ሲገዙ በሀገሩ ገንዘብ ተመንዝሮ ሊከፍሉ ይችላሉ። የቲኬቱ ዋጋ የሚወሰነው ቲኬቱን በሚገዙበት ቀን የሀገሩ ገንዘብ ባለው የዶላር የውጭ ምንዛሬ ተመን መሰረት ተሰልቶ ነው። ይህም ሁሉም አየር መንገዶች የሚጠቀሙበት ዓለም- አቀፋዊ አሠራር ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግብይታቸው በዶላር ለሚደረጉ የዓለም-አቀፍ በረራዎች ላይ ያደረገው የተለየ ለውጥ የለም፤ ይሁን እንጂ ዓለም-አቀፍ ቲኬቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በብር ሲገዙ ጭማሪ የሚያሳየው የዶላሩ ዋጋ አሁን ገበያ ላይ ባለው የብር የውጭ ምንዛሪ መጠን ስለሚቀየር ነው። ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ ቲኬት የሚሸጡ ሁሉም ዓለም-አቀፍ አየር መንገዶች የሚጠቀሙበት አሠራር መሆኑን ክቡራን ደንበኞቻችን እንዲረዱልን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።
በሌላ በኩል በሀገራችን በቅርቡ የተደረገውን የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያ ተከትሎ ለሀገር ውስጥ በረራ በቲኬት የብር ዋጋ ላይ እስከ አሁን የተደረገ ለውጥ የለም። ይሁን እንጂ ከአውሮኘላኖች የግዢ እና የኪራይ ዋጋ እንዲሁም ክፍያቸው በውጭ ምንዛሪ ከኾኑ የአውሮኘላኖች ጥገና እና የመለዋወጫ ዕቃዋች ግዢዎች ጋር ተያይዞ ወደፊት የሀገር ውስጥ በረራ የቲኬት ዋጋ ላይ በጥናት በተደገፈ መልኩ መጠነኛ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚችል ግንዛቤ እንዲወሰድ ከወዲሁ ለማሳሰብ እንወዳለን ማለቱን ከአየር መንገዱ የተገኘ መረጃ ያሳያል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!