ማኅበረሰቡ የሚሠሩ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በባለቤትነት እንዲጠብቅ ተጠየቀ።

18

ባሕር ዳር: ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ያለውን ሰፊ መልማት የሚችል መሬት፣ ውኃ እና የሰው ሃብት በተቀናጀ መንገድ ለመጠቀም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ የአማራ ክልል የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢንጂነር ዳኝነት ፈንታ (ዶ.ር) ገልጸዋል።

በ2016 በጀት ዓመት በጥናት እና ዲዛይን ሥራ ላይ ከነበሩ 93 ፕሮጀክቶች ውስጥ 29 ያህሉን፣ ከ129 የግንባታ ሥራዎች ውስጥ ደግሞ 77 ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ተችሏል ብለዋል። በ2017 በጀት ዓመት የክልሉን ጸጋዎች ታሳቢ ያደረገ ሥራ ለመሥራት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑንም ነው ቢሮ ኀላፊው የገለጹት። በበጀት ዓመቱ 110 ፕሮጀክቶች የጥናት እና ዲዛይን ሥራ የሚሠራ ይኾናል። 23 ሺህ 896 ሄክታር መሬት ማልማት የሚችል የፕሮጀክት ሰነድ ለግንባታ ዝግጁ ለማድረግም ታቅዷል።

ከዚህም ባለፈ 148 ነባር እና የአዳዲስ ፕሮጀክቶችን የግንባታ ሥራ ለማከናወን ታቅዷል፤ ከዚህም 7 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚችሉ 82 ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ በ2017/18 በጀት ዓመት ለልማት ክፍት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ባለፈው በጀት ዓመት የጥገና ሥራቸው የተጀመሩ 7 ፕሮጀክቶችንም ለማጠናቀቅ ትኩረት ተደርጓል።

የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው ጊዜ እና ጥራት ለማጠናቀቅ የኢንተርፕራይዞችን አቅም ማሳደግ እና መደገፍ፣ ድክመት ያለባቸውን ደግሞ የማስተካከያ ርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል። የጥናት፣ ዲዛይን እና የግንባታ የጥራት ችግሮችን መቀነስ አንዱ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው።

በክልሉ በመስኖ መልማት የሚችለውን መሬት አቅም ለመለየት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በፌዴራል መንግሥት እና በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች እየተጠኑ የሚገኙ የመስኖ ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲኾኑ ማኅበረሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችንም በባለቤትነት መጠበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደብረ ብርሃን ከተማ ሰላምን በዘላቂነት ለማስጠበቅ ነዋሪውን ያሳተፈ ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
Next articleየደብረ ብርሃን ዞናል መናኸሪያ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ በተደረገው ማሻሻያ የተሻለ አገልግሎት እያገኙ እንደኾነ ተገልጋዮች ተናገሩ።