
ደብረ ብርሃን: ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ በ2017 ዓ.ም የብሎክ አደረጃጀቶችን በመፍጠር የተገኘውን ሰላም ለማጠናከር ያለመ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል። በመድረኩ የቀበሌ እና የክፍለ ከተማ መሪዎች እና የጸጥታ አካላት የታደሙ ሲኾን በጸጥታ ሥራው የማኅበረሰቡ ድርሻ ትልቅ ግምት የሚሰጠው መኾኑ ተገልጿል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አበበ የአካባቢውን ነባራዊ ኹኔታ በማገናዘብ ዕቅዶችን ማውጣትና የብሎክ አደረጃጀቶችን ማጠናከር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ “የጸጥታ መዋቅሩን በማገዝ በኩል ነዋሪዎቹ ብርቱ ጉልበት ናቸው” ያሉት አቶ መኳንንት በጋራ መሥራት በሚቻልባቸው አማራጮች ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡
ሰላም ለነገ የምንለው ሳይኾን ዛሬ ላይ የምንፈጥረው እሴት በመኾኑ የጸጥታ አካላት ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀራርበው መሥራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡ የጸጥታ አካላት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት በመወጣት ማኅበረሰቡን ያሳተፈ እና ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው የተነገረው፡፡
በደብረ ብርሃን ከተማ ለጸጥታ ሥራ ነዋሪዎች ተሳትፎ የሚያደርጉበት 334 ብሎኮች የተደራጁ ሲኾን ከዚህ ውስጥ 134 የሚኾኑት በንቃት በተግባሩ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ ነው ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ስንታየሁ ኃይሉ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!