“የትምህርት ሥርዓቱን ችግር ከጸጥታው ጉዳይም አልፎ መመርመር ያስፈልጋል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

37

ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ሥርዓቱ የገጠመውን ስብራት ለመጠገን የሚያስችል የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ የትምህርት ዘርፉ ባለሙያዎች እና መሪዎች እየተሳተፉ ነው። ያለፈው ዓመት የክልሉ የትምህርት ሥርዓት እክሎች እና የቀጣይ ዓመት እቅድ ደግሞ የውይይቱ ማዕከል ናቸው።

“የነገዋ ኢትዮጵያ የዛሬ ተማሪዎቿን ትመስላለች” ያሉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ትምህርት ትውልድን በመቅረጽ ብቻ ሳይኾን ሀገር በመገንባት በኩል አበርክቶው ሰፊ ነው ብለዋል።

የትምህርት ሥርዓቱ ስብራት ያደሩ እና የተደራረቡ ችግሮች የፈጠሩት ነው ያሉት ኀላፊዋ ባለፉት ዓመታት የገጠሙን ውስብስብ የጸጥታ ሁኔታዎች ችግሩን እንዳባባሱት ግን አይዘነጋም ነው ያሉት። ችግሩን በጊዜ መፍታት ካልቻልን እና ባለበት ከቀጠለ ግን ርስታችንን እንጥላለን ነው ያሉት።

የትምህርት ውጤት የሚለካው ባለን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ሃብት ነው ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ በተማሪዎች ውጤት ላይ የተሻለ ነገር ማምጣት ካስፈለገ በብዙው ኢንቨስት ማድረግን ይጠይቃል ብለዋል። መዋዕለንዋዩም በጊዜ፣ በጉልበት፣ በዕውቀት እና በቁስ የሚለካ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ዶክተር ሙሉነሽ የትምህርት ሥርዓቱን ስብራት ለመጠገን የፖለቲካ አመራሩ እና የትምህርት ሴክተሩ ባለሙያዎች ቁርጠኛ፣ ጽኑ እና ለውጤት የሚተጉ መኾን አለባቸው ብለዋል።

ባለፈው ዓመት በክልሉ ለነበረው ዝቅተኛ የትምህርት ሥርዓት አፈጻጸም እና ስብራት ከጸጥታው ጉዳይም አልፎ መመርመር እንደሚያስፈልግ ዶክተር ሙሉነሽ አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደብረታቦር ከተማ በአሁኑ ሰዓት ያላትን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ማኅበረሰቡ የተለመደ አጋርነቱን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ተጠየቀ።
Next article“የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የተሟላ ሀገራዊ ዕድገት ያመጣል” ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች