ደብረታቦር ከተማ በአሁኑ ሰዓት ያላትን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ማኅበረሰቡ የተለመደ አጋርነቱን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ተጠየቀ።

16

ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል። ደብረታቦር ከተማ የበርካታ ታሪክ እና እሴቶች መገኛ የኾነች፣ በሀገር ግንባታ ታሪክ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አያሌ ጀግኖችን ያበቀለች ከተማ ናት።

ከተማዋ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በልማት እንቅስቃሴ ወደተሻለ ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ የምትገኝ ቢኾንም በክልሉ አጋጥሞ በቆየው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በሚፈለገው አግባብ ለማስኬድ አስቸጋሪ ኾኖ ቆይቷል ይላል።

የክልሉ መንግሥትም ኾነ የፌዴራሉ መንግሥት በአማራ ሕዝብ ጉዳይ ጥያቄ አለኝ የሚል አካል ካለ ለመወያዬት እና ለመደራደር ዝግጁነታቸውን ቢገልጹም ከስህተታቸው መማር ያቃታቸው እና የሕዝብ መከራ የማይገዳቸው አካላት በደብረታቦር ከተማ ዙሪያ በመሰባሰብ ትንኮሳ ለማድረግ እና ሕዝብን ለማሸበር ሞክረዋል ይላል መግለጫው።

ይሁን እንጂ ሕዝቡ ለሰላም ያለውን ጽኑ ፍላጎት በተደጋጋሚ ውይይቶች በማረጋገጡ እና የሰላሙ ባለቤት በመኾኑ እቅዳቸው በቀላሉ ሊከሽፍ ችሏል። ከተማን ለማውደም እና ሕዝብን ለማሸበር የመጣው ቡድንም በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በክልሉ የጸጥታ ኃይል እና በከተማው የጸጥታ መዋቅር ተመቶ ተመልሷል ይላል የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር መግለጫ።

ይህ አይነቱ የጥፋት መንገድ የቱንም ያህል ርቀት አያስጉዝም ያለው ከተማ አሥተዳደሩ በተሳሳተ መንገድ የተሰለፉ አካላት ወደ ሰላም በመምጣት የሕዝብን ስቃይ እንዲቀንሱ ጥሪ መቅረቡን ከከተማው ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በአሁኑ ሰዓት ከተማዋ በፍጹም ሰላማዊ እንቅስቃሴ የምትገኝ ሲኾን የከተማው ማኀበረሰብ የተለመደ የሰላም አጋርነቱን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል እንጠይቃለን ብሏል የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዓለም ምግብ ፕሮግራም ለመስኖ ልማት አገልግሎት የሚውሉ የሶላር ፓምፖችን ድጋፍ አደረገ።
Next article“የትምህርት ሥርዓቱን ችግር ከጸጥታው ጉዳይም አልፎ መመርመር ያስፈልጋል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)