የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለመስኖ ልማት አገልግሎት የሚውሉ የሶላር ፓምፖችን ድጋፍ አደረገ።

31

ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአማራ ክልል ለሚገኙ 12 ወረዳዎች ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው 120 የሶላር ፓምፖችን ድጋፍ አድርጓል። የሶላር ፓምፖቹ ተንቀሳቃሽ፣ ለአጠቃቀም ምቹ፣ ቀላል እና ወጪ ቆጣቢ መኾናቸውን የተናገሩት የሰልፈር ፋብሪካ የምሥራቅ አማራ ክላስተር አስተባባሪ ቸኮል ወልዴ ናቸው።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ደመቀ አድማሱ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከሰልፈር ፋብሪካ መንግሥታዊ ያልኾነ ድርጅት ጋር በጋራ በመኾን የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ምክትል ኀላፊው የዓለም ምግብ ፕሮግራም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ በማድረግ ረገድም በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ነው ያስገነዘቡት።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የደሴ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ሞገስ ታሪኩ ተቋሙ በዋናነት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በአደጋ ጊዜ በተፈጥሮ ወይም በሰው ሠራሽ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ሕይዎት የማዳን ሥራ እና ዜጎች ራሳቸውን በራሳቸው ማሥተዳደር እንዲችሉ ድጋፍ የማድረግ ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የተደረገው ድጋፍ ከጀርመን ልማት ባንክ የተገኘ መኾኑን የተናገሩት አስተባባሪው አርሶ አደሮች ዝናብን በመጠበቅ ብቻ ምርታማነትን ማሳደግ ስለማይቻል የተደረገው የሶላር ፓምፕ ድጋፍ አቅም ያለው በመኾኑ አርሶአደሮችን ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ፊኒክስ ሀየሎም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየወባ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።
Next articleደብረታቦር ከተማ በአሁኑ ሰዓት ያላትን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ማኅበረሰቡ የተለመደ አጋርነቱን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ተጠየቀ።