
ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ አካሂዷል። በግምገማው በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ለጤናው ዘርፍ ፈተና ኾኖ መቆየቱ ተነግሯል። በክልሉ የኮሌራ ወረርሽኝ እና የወባ በሽታ በስፋት መኖሩ ተገልጿል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ጅብሪል መርሻ በዞኑ የኅብረተሰብ ጤና ስጋቶች መኖራቸውን ተናግረዋል። በዞኑ ቋራ ወረዳ የኮሌራ ወረርሽኝ ተከስቶ እንደነበር የተናገሩት ኀላፊው የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ የመከላከል ሥራ መሠራቱን አስታውቀዋል። ተከስቶ የነበረውን ወረርሽኝ መነሻ በማድረግ በድጋሜ ለኅብረተሰቡ ስጋት እንዳይኾን እየተሠራ ነው ብለዋል።
ወባን የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን የተናገሩት ኀላፊው በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት ማድረግ አለመቻሉንም አንስተዋል። ግብረ ኀይል በማቋቋም የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራ እየተሠራ እንደኾነም አስረድተዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ አየለ አልማው የወባ ወረርሽኝ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ መከሰቱን ገልጸዋል። የወባ ወረርሽኙን ለመከላከል ወረዳዎች ዝግጅት እንዲያደርጉ መደረጉንም ተናግረዋል። 118 ሺህ የሚጠጉ ወገኖች በወባ በሽታ መያዛቸውንም ገልጸዋል። ወባን ለማጥፋት እየተሠራ ባለበት ወቅት በወረርሽኝ መልክ መከሰቱ አስደንጋጭ ነው ብለዋል። ሕሙማን ሕክምና እንዲያገኙ እና ጉዳት ሳይደርስባቸው ለመከላከል ርብርብ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
ሰዎች በወባ ከመያዛቸው አስቀድሞ ለመከላከል የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እንዲሠራ፣ የአጎበር አጠቃቀም እንዲሻሻል፣ ማኅበረሰቡ ራሱን እንዲከላከል ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። በቀጣይ ወራትም ከፍተኛ የወባ ስርጭት ሊኖር እንደሚችል የተናገሩት ኀላፊው ስርጭቱን ለመከላከል ከፍተኛ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። የወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ የኅብረተሰብ ጤና ችግሮችን ለመከላከል እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በክልሉ የኮሌራ እና የወባ ወረርሽኝ ስርጭት መኖሩንም ነው የተናገሩት። በምዕራብ ጎንደር ቋራ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባቲ ወረዳ የተከሰቱ የኮሌራ ወረርሽኞችን በከፍተኛ ርብርብ መቆጣጠር መቻሉን ያነሱት ዳይሬክተሩ በባሕርዳር ዙሪያ፣ በጎንደር ከተማ እና በዙሪያው ኮሌራ መከሰቱን ገልጸዋል። በምዕራብ ጎንደርም እንደ አዲስ ኮሌራ መከሰቱን ነው የተናገሩት።
ኮሌራ ሲከሰት አጋላጭ ምክንያቶችን የመለየት እና ፈጣን የኾነ የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ መኾኑንም ገልጸዋል። የቀን ተቀን ክትትል እየተሠራ እንደሚገኝም አመላክተዋል። የግንዛቤ ፈጠራ ሥራም ሌላኛው ሥራ መኾኑን ነው የተናገሩት። የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር፣ የንጽሕና አጠባበቅ አናሳ መኾን እና ሌሎች ኮሌራን ሊያባብሱ እንደሚችሉ ነው የተናገሩት።
በተለይም ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። የወባ በሽታ በተለየ መንገድ እየጨመረ መኾኑንም ተናግረዋል። ኢንስቲትዩቱ የወባ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በከፍተኛ ትኩረት እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። በተለይም ከመስከረም ጀምሮ ሊከሰት የሚችለውን የወባ በሽታ ታሳቢ ያደረገ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የክልሉን የወባ በሽታ ስርጭት ሽፋን 70 በመቶ የሚይዙ 34 ወረዳዎች መለየታቸውን ነው የተናገሩት። የክልሉን ከፍተኛ ሽፋን በሚይዙ ወረዳዎች ላይ ጠንካራ ሥራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። የሚከሰተውን የወባ በሽታ ከ50 በመቶ በታች ለመቀነስ ግብ ተይዞ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲዎችን፣ የወጣቶችኝ፣ የረጅ ድርጅቶችን፣ የሙያ ማኅበራትን እና የመንግሥትን ቅንጅት እንደሚጠይቅም ተናግረዋል።
የጤና ግብዓት በሰላማዊ መንገድ መድረስ እንዲችል ሁሉም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባውም አንስተዋል። የወባ በሽታ የተንሰራፋው የማኅበረሰቡ ተሳትፎ በመቀነሱ መኾኑንም ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ የወባ መራቢያ ቦታዎችን ማጽዳት እና ራሱን መከላከል ይገባዋል ነው ያሉት። የበሽታ ምልክቶች ሲኖሩም በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት መሄድ ይገባልም ባይ ናቸው። ከጤና ተቋማት የሚወጡ መረጃዎችን እና ማስጠንቀቂያዎችን መከታተል እና መተግበር ይገባል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በዓመቱ ውስጥ የኮሌራ በሽታ መከሰቱን ያነሱት ኀላፊው አሁንም በዘጠኝ ዞኖች የኮሌራ ወረርሽኝ መኖሩንም አመላክተዋል። የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል የንጽሕና አጠባበቅን ማስተካከል ይገባልም ብለዋል።
የውኃ አቅርቦት እንዲኖር ከክልሉ የውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በጋራ እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ወረርሽኙን ለመከላከል በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። የኮሌራ በሽታ እየቀነሰ መጥቷል፣ ነገር ግን አሁንም ዝናብ እና ጎርፍን ተከትሎ እንዳይባባስ ማኅበረሰቡ ራሱን መከላከል ይገባዋል ብለዋል።
በክልሉ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ወገኖች ለወባ በሽታ መጋለጣቸውንም አስታውቀዋል። የወባ ስርጭቱ ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ የኬሚካል ርጭት እጥረት፣ የአዲስ አጎበር ስርጭት አለመኖር ወባ እንዲጨምር አድርጎታል ነው ያሉት።
በክልሉ ከፍተኛ የወባ ስርጭት አለባቸው ተብለው ከተመረጡ 34 ወረዳዎች መካከል በ22ቱ የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ነው ብለዋል። ሌሎቹንም ለማዳረስ ተጨማሪ ኬሚካል ከጤና ሚኒስቴር እየጠየቁ መኾናቸውን አስታውቀዋል። 11 ወረዳዎች ላይም አጎበር እየቀረበ ነው፤ አሁንም ተጨማሪ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች ረጂ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
በተለይም የወባ በሽታ በስፋት በሚራራባቸው ወራት በትኩረት መሥራት ይገባል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ እና በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች በትኩረት መሥራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። በቀጣይ የኮሌራ ወረርሽኝ እና የወባ በሽታን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!