“በቀጣይ ሁለት ወራት ቅጽበታዊ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት እና የአነስተኛ ግድቦች ከመጠን ያለፈ መሙላት ሊከሰት ይችላል” የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

21

አዲስ አበባ: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሦስት ወቅቶች በልግ፣ መኸር እና ክረምት በየአራት ወራት ከፍሎ ትንበያዎችን የሚሰጠዉ የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የክረምት ወራትን የዝናብ ምጣኔ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ የክረምቱ ወቅት የመጀመሪያ ሁለት ወራት ከፍተኛ የዝናብ ምጣኔ የታየበት እንደነበር አንስተዋል። በሰኔ ወር ከ30 እስከ100፣ በሐምሌ ወር ደግሞ ከ30 እስከ 118 ሚሊ ሜትር የኾነ ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት መታየቱ በመግለጫዉ ተነስቷል።

ዋና ዳይሬክተሩ “የክረምት ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ከመደበኛ በላይ የዝናብ ምጣኔ ይጠበቃል” ብለዋል። ከእነዚህ ውስጥም አማራ፣ ትግራይ፣ ቤንሻንጉል፣ ጋምቤላ እና ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖርባቸዉ ይጠበቃል ነው ያሉት።

ዋና ዳይሬክተሩ በመግለጫዉ እንዳነሡት የታየዉ ከመደበኛ በላይ የዝናብ ምጣኔው ከግብርና አኳያ ዘግይተዉ ለተዘሩ ሰብሎች አመች ከመኾኑ በተጨማሪ ለአረንጎዴ አሻራ ሥራዎች ምቹ ነው። ኾኖም በተለያዩ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ከመደበኛ በላይ ዝናብ በመኖሩ የመሬት መንሸራተት፣ የአፈር መሸርሸር እና ማሳ ላይ ዉኃ የመተኛት ችግሮች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ከግብርና አኳያ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች እንዲሠሩ መልእክት ተላልፏል።

በክረምቱ የታየዉ ከፍተኛ የዝናብ መጠን በቀጣይ ሁለት ወራት ተጠናክሮ ሊቀጥል ስለሚችል ቅጽበታዊ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራት እና የአነስተኛ ግድቦች ከመጠን ያለፈ መሙላት ሊከሰት ይችላል፤ ለዚህም ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት በመግለጫዉ ተመላክቷል።

ዘጋቢ:- ቴዎድሮስ ኃይለየሱሥ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀገር የገጠማትን ስብራት በዘላቂነት ለመጠገን ትምህርት ላይ መሥራት ግድ ይላል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleየወባ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።