“ሀገር የገጠማትን ስብራት በዘላቂነት ለመጠገን ትምህርት ላይ መሥራት ግድ ይላል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

32

ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ሥርዓቱ የገጠመውን ስብራት ለመጠገን የሚያስችል የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።

ባለፈው ዓመት ክልሉ ያጋጠመውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የመማር ማስተማር ሥራው ተቋርጦ ቆይቷል። የምክክር መድረኩ ዓላማም ካለፈው ዓመት ውስንነቶች ተነስቶ እና ችግሮችን ለይቶ ለቀጣይ ዓመት የመማር ማስተማር ሥራ እቅድ ትግበራ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ነው ተብሏል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የነገዋ ሀገር የምትገነባው በዛሬዎቹ ተማሪዎች ትከሻ ላይ ነው ብለዋል። በተማሪዎች እና ትምህርት ላይ አልሞ መሥራት ትውልድ ላይ መሥራት መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

አማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በገጠሙት የሰላም እጦት ምክንያት ከተጎዱ ተቋማት መካከል የትምህርት ዘርፉ አንዱ ነው ብለዋል። ያለፈው ዓመት ደግሞ በውስጥ በገጠመን የፀጥታ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታ ተነጥለው የከረሙ ልጆች ቁጥር ከፍተኛ መኾኑንም አንስተዋል።

“ምናልባትም ዛሬ እንደሀገርም ኾነ እንደ ክልል የገጠመን ችግር የትምህርት ሥርዓቱ ስብራት ውጤት ሊኾን ይችላል፤ ሀገር የገጠማትን ስብራት በዘላቂነት ለመጠገን ትምህርት ላይ መሥራት ግድ ይላል” ነው ያሉት።

የትምህርት ዘርፉ መሪዎች፣ የወላጅ መምህራን ኅብረት፣ ምሁራን እና ሌሎች የሚመለከታቸው ዜጎች ሁሉ የትምህርት ሥርዓታችን የገጠመውን ስብራት ለመጠገን ተቀራርበው መምከር እንዳለባቸውም ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ አንስተዋል። ትላንት የገጠመን ችግር ነገም የሚፈትነን ከኾነ መሠረታዊ ክፍተት አለና በሚገባ መመርመር ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።

በቀሪ ጊዜያት የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን መጠገን፣ ግቢን ማስዋብ፣ የጎደለውን ለመሙላት የሚያስችል ሃብት ማሰባሰብ እና ተቀራርቦ መሥራት ይጠይቃል ነው ያሉት። የትምህርት ሥራ በአንድ ሴክተር ተሳትፎ ብቻ ዳር የሚደርስ ባለመኾኑ ሁሉንም ማስተባበር እና ማሳተፍን ይጠይቃልም ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በችግር ውስጥ ኾነንም 54 ፕሮጄክቶችን አጠናቅቀናል” አብዱልከሪም መንግሥቱ
Next article“በቀጣይ ሁለት ወራት ቅጽበታዊ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት እና የአነስተኛ ግድቦች ከመጠን ያለፈ መሙላት ሊከሰት ይችላል” የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት