“በችግር ውስጥ ኾነንም 54 ፕሮጄክቶችን አጠናቅቀናል” አብዱልከሪም መንግሥቱ

32

ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ አካሂዷል። በግምገማው በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ለጤናው ዘርፍ ፈተና ኾኖ መቆየቱ ተመላክቷል። የጤና ግብዓት በአግባቡ እንዳይቀርብ፣ የጤና መሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲስተጓጎሉ አድርጓል ነው የተባለው።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ጅብሪል መርሻ በዞኑ ባለው አንጻራዊ ሰላም የጤና ተቋሞች መደበኛ ሥራዎቻቸውን መቀጠላቸውን ተናግረዋል። ነገር ግን የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በቀበሌዎች ላይ ጫና ፈጥሯል ነው ያሉት። የግብዓት አቅርቦት ለማቅረብ የጸጥታ ሁኔታው በተወሰነ ጫና እንዳለውም አንስተዋል። በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ግን የገጠማቸው ችግር እንደሌለ ነው የተናገሩት።

የጤና ተቋማት ግንባታም መቀጠላቸውን ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ የተጠናቀቁ የጤና መሠረተ ልማቶች መኖራቸውንም አስታውቀዋል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ አየለ አልማው በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የጤና አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸውን ተናግረዋል። የጤና ግብዓት ለማቅረብ እና ለማሰራጨት ፈተና እንደኾነም ተናግረዋል። የኦክስጅን፣ ደም እና መድኃኒት ለማሠራጨት ተቸግረው መቆየታቸውንም ገልጸዋል።

በችግርም ውስጥ ኾነው የጤና ተቋማት መደበኛ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ጥረት መደረጉንም ተናግረዋል። የጤና ተቋማትን እና ባለሙያዎችን ለመደገፍ፣ የጤና መድኅን ሥራ እና የጤና መሠረተ ልማት ግንባታዎችን በሚፈለገው መንገድ ለመሥራት የጸጥታ ችግሩ ፈተና እንደኾነባቸውም አንስተዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ በ2016 በጀት ዓመት የሕይዎት አድን በመሥራት እና የጤና አገልግሎት ሥራዎችን ሳይቆራረጡ እንዲቀጥሉ በማድረግ የተሠራው ሥራ አበረታች ነው ብለዋል። የእናቶችን እና የሕጻናትን ሞት ለመቀነስ፣ የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል እና የክትባት አገልግሎት በመስጠት በኩልም ጥሩ ሥራ መሠራቱን ነው የገለጹት። ተላላፊ የኾኑ እና ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን በመከላከል እና በመቆጣጠር በኩልም በትኩረት ተሠርቷል ነው ያሉት።

የሰላም እና የጸጥታ ችግሩ ግን ለሥራቸው ፈተና ኾኖ መቆየቱን አንስተዋል። የጤና ኤክስቴንሽን ሥራው በጸጥታ ችግሩ ምክንያት መጎዳቱንም ተናግረዋል። የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በጸጥታው ምክንያት እንደፈለጉ መሥራት አለመቻላቸውን ነው የገለጹት። የጸጥታ ችግሩ የግብዓት አቅርቦት ላይ ጫና ማሳደሩንም ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ መድኃኒቶችን እና ሌሎች የጤና ግብዓቶችን ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል፡፡ ግብዓቶቹ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከአጋር አካላት እና ከጤና ቢሮ እንደተገኙ ነው ያስረዱት።

መድኃኒቶችን እና ሌሎች የጤና ግብዓቶችን ወደ ጤና ተቋማት ለማድረስ የጸጥታ ችግሩ ፈተና ኾኖባቸው መቆየቱን ነው ያነሱት። መድኃኒቶች እና ሌሎች ግብዓቶች መንገድ ላይ ይወሰዱባቸው እንደነበርም አንስተዋል። ጤና የማኅበረሰብ የሕይዎት ጉዳይ ነው ያሉት ኀላፊው ለማኅበረሰቡ የሕይዎት ጉዳይ ሁሉም በጋራ መቆም አለበት ብለዋል። የጤና ተቋማትንም መጠበቅ ይገባል ነው ያሉት።

341 ነባር ፕሮጄክቶች አሉን ያሉት ኀላፊው “54 ፕሮጄክቶችን በግጭት ውስጥ ኾነን አጠናቅቀናል” ብለዋል። በቅርቡ የሚጠናቀቁ ታላላቅ ሆስፒታሎች መኖራቸውንም ተናግረዋል። 287 ፕሮጄክቶች ወደ 2017 በጀት ዓመት መሸጋገራቸውንም አንሰተዋል። ከተሻገሩት ፕሮጄክቶች መካከል 25ቱ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ናቸው ተብሏል። ከታላላቆቹ መካከል ስምንቱ በጸጥታ ችግር ምክንያት እየተሠሩ አይደለም ብለዋል።

ቀሪዎቹ ፕሮጄክቶች በጥሩ የግንባታ ሂደት ላይ መኾናቸውንም አመላክተዋል። በጤና ዘርፉ መሠረታዊ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች መኖራቸውን መገምገማቸውን የተናገሩት ኀላፊው በቀጣይ አገልግሎትን በፍትሐዊነት እና በጥራት ለመስጠት ይሠራል ነው ያሉት። በጸጥታ ችግሩ የጤና መድኅን አገልግሎት መጎዳቱንም ተናግረዋል። በችግር ውስጥም ኾነው በጤና መድኅን 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ማሠባሠባቸውንም ገልጸዋል። የጤና መድኅን ተደራሽነትን ለማስፋፋት የተደረገው ጥረት በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ችግር ገጥሞት ቆይቷል ብለዋል። በ2017 በጀት ዓመት የጤና መድኅን ተደራሽነት በትኩረት ይሠራበታልም ነው ያሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት 116 አዳዲስ የገጠር ከተሞችን እና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ።
Next article“ሀገር የገጠማትን ስብራት በዘላቂነት ለመጠገን ትምህርት ላይ መሥራት ግድ ይላል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)