በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት 116 አዳዲስ የገጠር ከተሞችን እና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ።

9

ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መላኩ ታዬ እንዳስታወቁት በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት በገጠር እና በከተማ 426 ሺህ 290 አዳዲስ ደንበኞችን ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። በ2016 በጀት ዓመት የአዳዲስ ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች ቁጥር ከባለፈው 2015 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ75 ሺህ 729 ደንበኞች ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል።

ተቋሙ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት 100 የገጠር ከተሞችን እና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ መላኩ 116 አዳዲስ የገጠር ከተሞችን እና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል። እንደ አቶ መላኩ ገለጻ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እና የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ እየተሠራ ነው። በዚህም ፕሮጀክት ተቀርጾ 50 ሺህ ነባር ቆጣሪዎች በስማርት ቆጣሪዎች በመቀየር ላይ ይገኛሉ።

እስካሁን 36 ሺህ 700 ነባር ቆጣሪዎችን በስማርት ቆጣሪዎች መቀየር ተችሏልም ብለዋል። ነባር ቆጣሪዎቹ በስማርት ቆጣሪ የመቀየሩ ሥራ በተለይ አገልግሎቱን ለማዘመን ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል። በተያዘው በጀት ዓመትም የኤሌክትሪክ ተጠቃሚውን ቁጥር ለማሳደግ እና አገልግሎት አሰጣጡን የበለጠ ለማዘመን ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ነው አቶ መላኩ ያብራሩት።

በበጀት ዓመቱ በተቋሙ አዳዲስ ደንበኞች ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ከማስቻል በተጨማሪም የተበላሹ የኤሌክትሪክ ማሠራጫ ማዕከላት እድሳት መደረጉን አክለዋል። እንደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘገባ ኤሌክትሪክ በማይደርስባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች የሌሎች የኃይል አማራጭ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አቶ መላኩ ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ550 ቢሊየን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት ለማፀደቅ ለምክር ቤቱ ሊቀርብ ነው” ኢዮብ ተካልኝ (ዶ.ር)
Next article“በችግር ውስጥ ኾነንም 54 ፕሮጄክቶችን አጠናቅቀናል” አብዱልከሪም መንግሥቱ