
ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለ2017 በጀት ዓመት ከ550 ቢሊየን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለማፀደቅ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ፡፡ የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ.ር) የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራውን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ የፖሊሲ ማሻሻያው ዘላቂና አስተማማኝ ኢኮኖሚ ለመገንባት መሠረት የሚጥል መኾኑን አስረድተዋል፡፡
የፖሊሲ ማሻሻያው ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ የተለያዩ የፋይናንስ ምንጮች ድጋፍ እያደረጉ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ገንዘብ ሚኒስቴር ለ2017 በጀት ዓመት ይፋ ካደረገው የፌዴራል መንግሥት በጀት ተጨማሪ በጀት እንደሚያፀድቅ አመላክተዋል፡፡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለማፀደቅ የተዘጋጀው ከ550 ቢሊየን ብር በላይ መኾኑንም ነው የገለጹት። ከዚህ ወስጥ 240 ቢሊየኑ ለማኅበራዊ ልማት የሚውል ነው ብለዋል።
መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲውን በተሟላ መልኩ ገቢራዊ ሲያደርግ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ታሳቢ በማድረግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በዚህም ቋሚ ገቢ ያላቸውና በልማታዊ ሴፍቲኔት ለሚታገዙ ዜጎች በቂ ድጎማ ለማድረግ ተጨማሪ በጀቱ ወሳኝ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
ተጨማሪ በጀቱ ለዘይት፣ ለነዳጅና ለመድኃኒት ድጎማ እንዲውል በማድረግ በፖሊሲው ትግበራ ጊዜ ሊደርሱ የሚችሉ ስጋቶችን አስቀድሞ ለመከላከል እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል፡፡ ኢዜአ እንደዘገበው ከዚህ ባለፈ ሀገራዊ ወጪን በራስ ገቢ ለመሸፈን የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የፖሊሲ ትግበራው የገቢ አቅምን በማሳደግ በኩል ወሳኝ ሚና እንዳለውም ነው ያነሱት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!