“ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አሠራሮች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው” ግብርና ቢሮ

16

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2016/17 የምርት ዘመን ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን 169 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት እየተሠራ ይገኛል። የአማራ ክልል ክልል ግብርና ቢሮ ከገጠር ክላስተር ተቋማት ጋር በ2016 የምርት ዘመን የሥራ አፈጻጸም እና በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ ላይ ከዞን የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

በክልሉ በዘር ለመሸፈን ከታቀደው መሬት ውስጥ እስከ አሁን 87 በመቶ በዘር መሸፈኑን በምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ገልጸዋል። በምርት ዘመኑ ምርታማነቱን በሄክታር ከነበረው 28 ነጥብ 2 ወደ 32 ነጥብ 7 ኩንታል ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) እንዳሉት እቅዱን ለማሳካት ከበፊቱ በተለየ መንገድ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ እየተሠራጨ ይገኛል። ለዚህም እስከ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ መሠራጨቱን በማሳያነት አንስተዋል። የተሰራጨው ማዳበሪያም በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል የክትትል ሥራ እየተሠራ እንደኾነ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ምርታማነትን ለማሳደግ 800 ሺህ ሄክታር መሬት በትራክተር ማረስ ተችሏል። በሰብል ስብሰባ ወቅት ሊያጋጥም የሚችለውን ብክነት ለመቀነስ ኮምባይነር ለመጠቀም ዝግጅት መደረጉንም አንስተዋል። አርሶ አደሩ ሙሉ ፓኬጅ እንዲተገብር እየተደረገ መኾኑንም ጠቅሰዋል። እስከ አሁን የተሻለ የዝናብ ሥርጭት መኖሩንም ነው የገለጹት። በምርት ዘመኑ አጠቃላይ የግብርና ሥራው ከባለፉት ጊዜያት የተሻለ በመኾኑ በሄክታር ለማግኘት የታቀደውን ምርት ማሳካት እንደሚቻል ገልጸዋል።

በ2017 የምርት ዘመን ተቋማቱ ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር በእውቀት ላይ የተመሠረተ፣ ውጤት ሊያመጣ የሚችል እና የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ያደረገ ዕቅድ በማቀድ ወደ ሥራ መግባት እንደሚገባም አሳስበዋል። ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) አክለውም የድህረ ምርት አያያዝ ላይ ትኩረት ማድረግ፣ የኩታ ገጠም ልማትን ማስፋት እንዲሁም የአርሶ አደሮች የማሠልጠኛ ማዕከላትን ማጠናከር ይገባልም ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ18 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ሴቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ የክልሉ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።
Next article“ከ550 ቢሊየን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት ለማፀደቅ ለምክር ቤቱ ሊቀርብ ነው” ኢዮብ ተካልኝ (ዶ.ር)