ከ18 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ሴቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ የክልሉ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

36

ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቢሮው ከዞን መሪዎች፣ ተጠሪ ተቋማት እና ልዩ ልዩ አጋሮች ጋር በ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ አካሄዷል።

በውይይት መድረኩ ላይ የቢሮው ኃላፊ ብርቱካን ሲሳይ እንዳሉት በ2016 የሥራ ዘመን ፆታዊ ጥቃት እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች መረጃ በመለየት የሥነ ልቦና፣ የጤና ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ በገቢ ማስገኛ ሥራዎች እንዲሰማሩ ተደርጓል። ከ18 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ሴቶች 13 ሚሊዮን ብር በመመደብም ወደ ቋሚ የሥራ ዕድል ማስገባት መቻሉን ቢሮ ኃላፊዋ ተናግረዋል።

በቢሮው የታቀፉ ፕሮጀክቶች ክልሉ በገጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለቅቀው እንዳይወጡ ተደጋጋሚ የማግባባት ውይይቶች በማድረግ በያዙት ሐብት ብዙ ሰዎችን ተጠቃሚ ኾነዋል ነው ያሉት። ሴቶችን፣ አረጋውያንን፣ ሕጻናትን እና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ኹነቶችን ከማክበር ባለፈ ግንዛቤ በመፍጠር ችግር ውስጥ ያሉትን በመርዳት የሚታይ ለውጥ መጥቷል ብለዋል።

ከሰሜኑ ጦርነት እና አሁን ክልሉ ከገጠመው ግጭት ጋር ተያይዞ የበርካታ ሕጻናትን ሕይዎት መታደግ መቻሉን ቢሮ ኃላፊዋ በአብነት አስቀምጠዋል። በቀጣይም ችግር ውስጥ ያሉ ሕጻናትን ተቀብሎ መንከባከብ የሚያስችል ባለአንድ ፎቅ ሕንጻ እየተገነባ መኾኑንም ወይዘሮ ብርቱካን ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል በገጠመው ጦርነት እና ድርቅ የተነሳም የተከሰተውን ችግር ለማለፍ ቢሮው ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር 118 ሚሊዮን ብር በመመደብ ለችግሩ ሰለባዎች ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል። ይሁንና በከልሉ በገጠመው ጦርነት እና ግጭት ምክንያት የፆታዊ፣ ማኀበራዊ እና የምጣኔ ሐብታዊ ተጎጂዎች ቁጥር በርካታ በመኾኑ ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣሙን ኃላፊዋ ገልጸዋል። በ2017 ዓ.ም ሰፊ ሥራ በመሥራት ተረጅነትን ለመቀነስ እና የሥራ ዕድልን የማሥፋት ሥራ ይከናዎናል ብለዋል።

ሴቶች የሰላም ባለቤት በመኾናቸውም 1ነጥብ 7 ሚሊዮን በከልሉ ነዋሪ የኾኑ ሴቶችን በማወያዬት ለሰላም መስፈን ድርሻቸውን እንዲወጡ መሠራቱን ቢሮ ኃላፊዋ አብራርተዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኀበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ የሮምነሽ ጋሻውጠና እንዳሉት የሰላም እጦት ቢኖርም ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመታደግ ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ የሰብዓዊነት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። እንደ ዞንም 83 ሺህ ለሚኾኑ ሴቶች በሰላም ዙሪያ በጉባኤ ማወያዬታቸውን ገልጸዋል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ1ሺህ 500 በላይ ሕገ ወጥ ተዘዋዋሪዎች ወደ መጡበት መመለሳቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ አስታወቀ።
Next article“ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አሠራሮች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው” ግብርና ቢሮ