
ገንዳ ውኃ: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የስደተኞች መገኛ እና መዳረሻ ሀገር ብቻም ሳትኾን መሸጋገሪያም ነች። ሕገ ወጥ ተዘዋዋሪዎች ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት ለመሄድ ከሚሸጋገሩባቸው የሀገሪቱ ጠረፋማ አካባቢዎች መካከል የአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው።
ምዕራብ ጎንደር ዞን ከጎረቤት ሀገር ሱዳን ጋር ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ የሚያዋስን ድንበር ሲኖረው ከ19 በላይ የሚኾኑ የሕገ ወጥ ተዘዋዋሪዎች እና አዘዋዋሪዎች መግቢያ እና መውጫ በሮች እንዳሉት በዞኑ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ የግጭት አፈታት እና የሰላም እሴት ግንባታ ቡድን መሪ ዮናስ ጋዲሳ ለአሚኮ ገልጸዋል። ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተነስተው በሱዳን በኩል አድርገው ለመውጣት በርካታ ወጣቶች ወደ ምዕራብ ጎንደር ዞን እንደሚመጡም አንስተዋል፡፡
አብዛኞቹ ሕገ ወጥ ተዘዋዋሪዎች ከሶማሌ፣ ኦሮሚያ፤ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እንደሚመጡ አቶ ዮናስ ተናግረዋል። ተዘዋዋሪዎቹ በተለይም በመተማ፣ ቋራ እና ምዕራብ አርማጭኾ ወረዳዎች በኩል በሚገኙ መውጫ በሮች እንደሚሻገሩ የጠቆሙት አቶ ዮናስ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ከ1ሺህ 500 በላይ ተዘዋዋሪዎች ለመውጣት ሲሉ መያዛቸውን ተናግረዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 722 ወንዶች ሲኾኑ 801 የሚኾኑት ሴቶች ናቸው ብለዋል። በዞኑ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ፣ ዓለም አቀፉ የሥደተኞች ተቋም (አይ.ኦ.ኤም) እና ሌሎች መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ተዘዋዋሪዎቹ ወደ መጡበት ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ነው የተናገሩት።
ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም እና በሰዎች የመነገድ ወንጀልን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ነውም ብለዋል። ይሁን እንጅ ተቆራርጦ በመሥራት በኩል ክፍተቶች እንዳሉ ነው አቶ ዮናስ የጠቆሙት።
ቡድን መሪው እንደገለጹት በተደረገ ክትትል እና ቁጥጥር 50 የሚኾኑ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች እና ደላሎች በሕግ ቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል፡፡ ከእነዚም መካከል 45ቱ ወንድ ሲኾኑ 5ቱ ሴቶች ናቸው፡፡ በፖሊስ በኩል 42 ክሶች ተመሥርተው 16ቱ ውሳኔ ያገኙ ሲኾን ሌሎቹ በሂደት ላይ ናቸው፡፡ በ16 የክስ ውሳኔም ከ7 ዓመት እሰከ 25 ዓመት የእስራት ቅጣት መወሰኑንም ጠቁመዋል።
በዞኑ በሰዎች በመነገድ ወንጀል የተሰማሩ ግለሰቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መኾኑን የጠቀሱት ቡድን መሪው ተዘዋዋሪዎችን ከፍተኛ ብር በማስከፈል እያሻገሩ ነው ብለዋል። አንዳንድ የጸጥታ መዋቅር አባላት በሰዎች የመነገድ የወንጀል ድርጊት ተዋናይ ኾነው መገኘታቸውን ያረጋገጡት አቶ ዮናስ እነዚህ አካላት ከመሰል ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ኅብረተሰቡ ወንጀለኞችን ለሕግ አጋልጦ ከመስጠት ባሻገር የፍትሕ እና የጸታ አካላት በቅንጅት ቁርጠኛ ኾነው መሥራት አለባቸው ብለዋል። ከሌሎች ክልሎች ከሚመጡ ወጣቶች ባሻገር በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙ በርካታ ታዳጊ ወጣቶች በጎረቤት ሀገር ሱዳን አድርገው እየወጡ እንደኾነም ተጠቁሟል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!