
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በየደረጃው ያሉ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ ተቋማት በማክሮ ኢኮኖሚ የትኩረት ጉዳዮች ዙሪያ እየመከሩ ነው። በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የሥራ እድል ፈጠራ እና የኑሮ ውድነትን መቀነስ የበጀት ዓመቱ የትኩረት መሥክ ናቸው ብለዋል።
የሥራ እድል ፈጠራም ኾነ የኑሮ ውድነት ቅነሳ ስለምንመኘው ብቻ የሚመጣ አይደለም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የመሪነት ሚናችን እና የሕዝብ ተቆርቋሪነታችን የሚገለጥበት ብርቱ ጥረትን ይጠይቃል ነው ያሉት። በተለይም የፖለቲካ መሪው ሊመራበት ይገባል ያሉትን የሥራ መርህ በዝርዝር አስቀምጠዋል።
መሪነታችሁ ከግብረ ገብነት እና ከሥነ ምግባር የመነጨ ሊኾን ይገባል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ቅቡል ባሕሪ እስካለን ድረስ የምንመራው ሕዝብ የነገርነውን የሚሰማ እና ለተግባራዊነቱም የሚተባበር ይኾናል ብለዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ በንግግራቸው የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኛ፣ ታታሪ እና ለሕዝብ ጥቅም የሚቆረቆር መኾን እንዳለበት ጠቁመው “እንደ መሪ በየደረጃው ያለን አመራሮች በክልላችን ጉዳይ ኀላፊነት መውሰድ አለብን” ነው ያሉት። ለሚፈጠር ችግር ባለቤት ከመፈለግ እና በድህረ ችግር ትንታኔ ከመጠመድ ወጥቶ በኀላፊነት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የክልሉ መሠረታዊ ችግሮች የሚመነጩት ከምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች ነው። ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮቻችን ለመሻገር ሃብት መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ንግድ፣ ትራንስፖርት፣ ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂን ማቀናጀት ያስፈልጋል ብለዋል። ገቢ የመሰብሰብ ጉዳይም በቀጣይ ዓመት በትኩረት የሚፈጸም ጉዳያችን ነው ብለዋል።
ሃብት ከማሰባሰብ ባሻገር ከእለት ፍጆታ የተሻገረ ሃብት ማከማቸት ላይ አቅዶ መሥራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን እና የከተሞችን መስፋፋት (ክትመትን) በአግባቡ መምራት ይኖርብናል ያሉት ርእሰ መሥተዳድ፤ የተገራ እና መጻዒውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ ክትመትን አውን እናድርግ ብለዋል።
ሰላም እና ጸጥታን ማስከበር ሌላው ትኩረት መሰጠት ያለበት ጉዳይ እንደኾነም አንስተዋል። በቀጣይ ጊዜያት ለአመራሩ አፈጻጸም ላይ የተመሠረተ ተጠያቂነት እና እውቅና እንደሚኖርም አንስተዋል። የሥራ እድል ፈጠራ እና ድህነት ቅነሳ ደግሞ አመራሩ የሚለካባቸው ቁልፍ ጉዳዮች ስለመሆናቸው አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!