
ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ እያካሄደ ነው። በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ጤና የሰውን ልጅ አዕምሯዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ አካላዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት የሚረጋገጥበት ነው ብለዋል። ጤና የሰው ልጅ ከጽንሰት እስከ ዕድገት የሚገነባበት መኾኑንም አስታውቀዋል።
በዓለም ጤና ድርጅት አሠራር መሠረት የጤና ሥርዓቱን በስድስት መሠረታዊ ምሰሶዎች ለማጽናት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የጤና አመራር ሥርዓትን እና መልካም አሥተዳደርን ማስፈን፣ የሰው ኃይልን ብቁ ውጤታማ እና ምርታማ ማድረግ፣ የጤና ፋይናንስ ሥርዓትን የማይበገር ማድረግ፣ የመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያ እና ሌሎች ግብዓቶች አቅርቦት፣ ሥርጭት እና አሥተዳደር ሥርዓቱን ማሻሻል፣ የጤና መረጃ ሥርዓትን በቴክኖሎጂ ማዘመን፣ የጤና አገልግሎትን ፍትሐዊነት፣ ጥራት እና ዘላቂነትን ማረጋገጥ የጤና መሠረታዊ ምሰሶዎች መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
የጤና መሠረታዊ ምሰሶዎችን በተጨባጭ ለማረጋገጥ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የጤና ሥርዓቱን የተሻለ ለማድረግ በጥናት የታገዘ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ብቁ የጤና ባለሙያዎችን እና መሪዎችን ለማፍራት እየተሠራ ነው ብለዋል። አላሠራ ያሉ አሠራሮችን ማሻሻላቸውንም አስታውቀዋል።
ከ2018 እስከ 2022 የአምስት ዓመት የስትራቴጂክ ዕቅድ መዘጋጀቱንም አመላክተዋል። የጤና ሥርዓቱን የዘመነ ለማድረግ በዲጂታል የታገዘ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። መረጃ ላይ የተመሠረተ የጤና ሥርዓት ፍትሐዊ እና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል።
ማኅበረሰብን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች መሥራታቸውንም ገልጸዋል። የአልትራሳውንድ አገልግሎት በ132 የጤና ተቋማት ላይ ማድረሳቸውን ተናግረዋል። የመድኃኒት እጥረቶችን እና የዋጋ አለመመጣጠንን ለማስተካከል የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤቶች እየተገነቡ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤቶች መስፋት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል።
መሪዎች ታላቅ ነገርን የሚያስቡ፣ የአስተሳሰብ አድማሳቸውን ያሰፉ የተግባር ሰው መኾን እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል። ከመሪዎች ያልታየውን የማየት እና የማሳየት፣ ያልተዳረሰውን የማዳረስ፣ በታማኝነት እና በታታሪነት መሥራት ይጠበቃልም ብለዋል። ባለፉት ዓመታት በኮሮና ቫይረስ፣ በሰሜኑ ጦርነት፣ በውስጥ ግጭት እና ሌሎች ችግሮች የጤና ዘርፍ መፈተኑን ያነሱት ኀላፊው በችግር ውስጥም ኾነው በአይበገሬነት መሠራቱን ተናግረዋል። አይበገሬ የጤና ሥርዓት እንዲኖር ላደረጉ አካላትም ምሥጋና አቅርበዋል።
ስኬቶችን የበለጠ ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር፣ ድክመቶችን ደግሞ ማስተካከል በቀጣይ ይጠበቃል ነው ያሉት። ዘመኑን የሚመጥን የጤና ተቋማትን መፍጠር እንደሚጠበቅም አመላክተዋል። የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። የጤና አገልግሎቶች ሳይቆራረጡ በተሟላ መንገድ ለመስጠት ዝግጅት ማድረግ ይገባል ብለዋል። በእልህ፣ በቁጭት እና በአንድነት ለማኅበረሰብ ጤና መሻሻል መትጋት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!