
ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በየደረጃው ያሉ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ ተቋማት በማክሮ ኢኮኖሚ የትኩረት ጉዳዮች ዙሪያ እየመከሩ ነው።
በምክክር መድረኩ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ ከዞን፣ ከተማ አሥተዳደር እና ወረዳዎች የተውጣጡ የዘርፉ መሪዎች ተሳታፊ ናቸው።
የአማራ ክልል ላለፉት ዓመታት በግጭት ውስጥ የቆየ ክልል ነው ያሉት ዶክተር አሕመዲን ሙሐመድ ሃብት መፍጠር፣ ማሠባሠብ እና ገቢ ማመንጨት ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል። ምርታማነትን ማሳደግ አስፈላጊ እንደኾነም ተናግረዋል። ከምርት የሚገኝ ገቢ ላይ ትኩረት መስጠት አንደሚገባም አንስተዋል።
ክልሉ ላለፉት ዓመታት የገጠመው ችግር ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኘው ሃብት ሲያመነጭ እና ኀይል ሲያሠባሥብ ነው ያሉት ኀላፊው ለዚህ ደግሞ ሕገ ወጥነትን መከላከል እና መቆጣጠር የፖለቲካ መሪዎች ተቀዳሚ ተልዕኮ ሊኾን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኢንዱስትሪን ማስፋፋት እና ከተሜነትን ማዘመን የሚቻለውም ሕገ ወጥነትን በመከላከል በመኾኑ በየደረጃው ያለው መሪ ለተፈጻሚነቱ በትጋት እንዲሠሩ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!