
ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ከተዋረድ እና ከሚያስተባብራቸው ተቋማት ጋር በ2017 በጀት ዓመት ዕቅዶች ላይ ውይይት አድርጓል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው በክልል ደረጃ ውይይት የተደረገበት የምጣኔ ሃብት፣ የማኅበራዊ ልማት እና ዘላቂ ሰላም የማስፈን እቅድን ለመተግበር የአሥተዳደር ዘርፉ አስፈላጊ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
ወደፊት እያንዳንዱ ድርሻው ምን መኾን እንዳለበት ዐውቆ እንዲሠራ የማስተባበርን አስፈላጊነት ጠቅሰው የቢሮው እና የክላስተሩ ተቋማት የመቶ ቀን እቅድ ወደታችኛው ደረጃ ወርዶ በተደጋጋሚ መገምገሙን ኀላፊው ገልጸዋል። ከእቅድ እና ውይይትም ባሻገር ወደ ተግባር መገባቱን የገለጹት አቶ ደሳለኝ በዚህ መድረክም ያንኑ እቅድ የበለጠ በማዳበር በጋራ ኀላፊነትን ለመወጣት ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል። በ2017 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ ላይ ደጋግመን መወያየታችን ኀላፊነታችንን በጋራ ለመወጣት ያስችለናል ብለዋል። የተሻለ ውጤት እየተገኘበት መኾኑንም ገልጸዋል።
አቶ ደሳለኝ በክልል ደረጃ እየተደረገ ባለው ጉባኤ የምጣኔ ሃብት፣ የማኅበራዊ እና የመልካም አሥተዳደር እቅዶች በምን መልኩ መፈጸም እንዳለባቸው እና የቅንጅት አሠራሩ ምን መምሰል እንዳለበት አቅጣጫ መሰጠቱን ጠቁመዋል። የታቀዱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች እንዲሳኩ የአሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር ጠንክሮ እንደሚሠራ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ተናግረዋል።
ውይይቱ ቀጥሎም የቢሮው ዓመታዊ እቅድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው። በክላስተሩ ሥር የሚካተቱ ተቋማትም እቅዳቸውን አቅርበው ውይይት እንደሚደረግበት ይጠበቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!