“ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ በተቀናጀ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር)

35

ባሕር ዳር: ሐምሌ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) የተመራ የፌዴራል እና የክልል የንግድ ሴክተር የሥራ ኅላፊዎች ቡድን በአዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ በመገኘት ከውጭ እየገባ ያለውን የፍጆታ እቃዎች ተመልክቷል።

በአዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ እና በሌሎች የጉምሩክ ቅርንጫፎች የፍጆታ ዕቃዎችን ጭነው የቆሙ ከ1ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ምርቱን ዛሬ እና ነገ ወደ ገበያ እንዲያስገቡ ሥራ ይጀመራል ነው ያሉት ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) ። በዚህም የገበያን ፍላጎት ከመሙላት ባለፈ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት በገበያ ላይ የተትረፈረፈ ለማድረግ 14 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ግዥ ተፈፅሞ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ይገኛል ብለዋል። በዚህም የምግብ ዘይት ምርቱ በማከማቻ መጋዘኖች ሳይራገፍ ቀጥታ ወደ ክልሎች ለማጓጓዝ የሚያስችል መዋቅር መዘርጋቱንም ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) ገልጸዋል።

የንግዱ ማኅበረሰብ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረው እና የተፈጠረውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት የሁሉም ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የንግድ ቢሮዎች እና የግብርና ሴክተሮች ግንዛቤ እየሰጡ ይገኛሉ ነው ያሉት ። በዚህም የገበያ ሁኔታን አስተማማኝ የማድረግ ሥራ ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የገለጹት ሚኒስትሩ “በፍጆታ ዕቃዎች ላይ ለዋጋ ጭማሪ የሚያበቃ ምንም ምክንያት የለም” ብለዋል።

በመኾኑም ምክንያታዊ ያልኾነ የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው የብረት፣ ሲሚንቶ፣ ቆርቆሮ እና ሌሎች የግንባታ ዕቃዎችን ጨምሮ የፍጆታ ምርቶች ከውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያ እና ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ይፋዊ ትግበራ በፊት በነበረው ዋጋ ነው መቀጠል ያለባቸው ብለዋል።

“ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ በተቀናጀ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ያሉት ሚኒስትሩ በእስካሁኑ ሂደትም 2ሺህ 20 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል። የኢዜአ ዘገባ እንደሚያሳየው በምንም መልኩ ዋጋ ለመጨመር የሚያበቃ ምክንያት ባለመኖሩ ከማሸግ ባለፈ የንግድ ፍቃዳቸውን መሰረዝ እና ከንግዱ መስመር እንዲወጡ የማድረግ ሥራ በዘላቂነት ይሠራል ብለዋል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር)።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደሴ ከተማ አሥተዳደር ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መኾኑ ተገለጸ።
Next article“ጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል” የኮሌጁ ዲን ተስፋሁን መኮንን