
ባሕር ዳር: ሐምሌ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ከጅምላ አከፋፋይ ነጋዴዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ሰይድ ካሳው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ምክንያት በማድረግ ያለአግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ጅምላ አስመጭ እና አከፋፋይ ነጋዴዎች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል። ይህ አግባብነት የለውም ያሉት አቶ ሰይድ ካሳው ነጋዴዎች የምታመጧቸውን ምርቶች እና ሸቀጦች በተመጣጠነ ዋጋ በመሸጥ ገበያውን የማረጋጋት ሥራ መሥራት አለባችሁ ብለዋል። ወደፊት የምታስመጧቸውን ምርቶች ከከተማ አሥተዳደሩ እና ከንግድ መምርያው በሚወርደው አቅጣጫ መሠረት መሸጥ ይኖርባችኋል የሚል መልእክትም አስተላልፈዋል።
ነጋዴዎች በሰጡት አስተያየት ምርቶችን እና ሸቀጦችን ከውጭ እና ከአዲስ አበባ በምናስመጣበት ጊዜ ያለአግባብ የተለያዩ ወጭዎችን ስለምንከፍል ሊስተካከልልን ይገባል ብለዋል። በተጨማሪም ሕዝብን ላልተገባ የኑሮ ውድነት የሚዳርጉ ተግባራትን እንደሚያስወግዱም ነጋዴዎች ተናግረዋል።
ከደሴ ከተማ አሥተዳደር ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በከተማዋ የተቋቋመው የገበያ አረጋጊ ግብረ-ኀይሉ በ5ቱም ክፍለ ከተሞች የመስክ ክትትል በማድረግ የዶላር ምንዛሬ እየጨመረ ነው በሚል ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ላይ እርምጃ እየተወሠደ ነው።
የማክሮ ኤኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ እና ምርቱን በደበቁ ነጋዴዎች ላይ ኅብረተሠቡ ጥቆማ እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቦል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!